
ጎንደር: ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት የመጓተት ታሪኩ አብቅቶ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ጥብቅ የሥራ ክትትል እንደሚደረግበት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገልጸዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በጎንደር ከተማ ተገኝተው የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። የጉብኝቱ ዓላማም የሥራዎችን እንቅስቃሴ በመመልከት እና ጥብቅ ክትትል በማድረግ በቀጣይም በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ለማስቻል ነው ብለዋል።
የመገጭ መስኖ ግድብ፣ የአጼ ፋሲል አብያተ መንግሥት እድሳት እና የጎንደር ከተማ የኮሪደር ልማትን ተመልክተዋል።
የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት ከ14 ዓመታት በላይ የመጓተት ታሪክ ያለው እና የአዝጋሚ አፈጻጸም ምሳሌ ነበር ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
መገጭ የፕሮጀክት መጓተት ምሳሌ መኾኑ አብቅቷል ነው ያሉት። አኹን ላይ በባለሙያዎች እና በሥራ ኀላፊዎች ከፍተኛ ተነሳሽነት እየተሠራ ነው፣ በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆም ወደ ልማት ይገባል ነው ያሉት።
ፕሮጀክቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከዓመት በፊት በጎንደር ተገኝተው በሰጡት አቅጣጫ መሠረት በተነሳሽነት ሥራው የተጀመረ እና የክልሉ መንግሥትም ከፍተኛ ክትትል የሚያደርግበት ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ።
መገጭ ከነበረበት ታሪክ ወጥቶ ባስቸኳይ እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ተናግረዋል። ለዚህም ከፍተኛ የኾነ የሰው ኀይል እና የማሽን አቅርቦት ተሟልቶለት እየተከናወነ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!