
እንጅባራ: ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ከ560 በላይ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ በልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በመታቀፍ በተለያዩ ዘላቂ የሃብት ማስገኛ ሥራዎች ሲሳተፉ ቆይተዋል። የከተማ ጽዳት፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የአካባቢ እንክብካቤ እና የከተማ ግብርና ደግሞ አባላቱ ሲሳተፉባቸው የነበሩ የሥራ መስኮች ናቸው።
ከተማ አሥተዳደሩ የአባላቱን የገቢ አቅም ይበልጥ ለማሳደግ በሴፍትኔት ፕሮግራም ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ በሚኾን ወጭ የተገነባ ሸድ ለ21 አባላት በዕጣ አስተላልፏል። የእንጅባራ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ የኔዓለም ዋሴ ላለፉት አራት ዓመታት ገደማ በከተማ አሥተዳደሩ የተተገበረው ልማታዊ ሴፍትኔት ዜጎች ጥሪት እንዲቋጥሩ ከማስቻሉ ባሻገር የዜጎችን የሥራ ባሕል የቀየረ መኾኑን ተናግረዋል።
ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ከተረጅነት ማላቀቅ እና ማኅበራዊ ፍትሕን ማረጋገጥ የቀጣይ የመንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ እንደሚኾንም ከንቲባው ገልጸዋል። የመስሪያ ቦታ የተመቻቸላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በተደረገላቸው ድጋፍ ከገቡበት ችግር ወጥተው ራሳቸውን መቻል እንደሚጠበቅባቸውም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አስገንዝበዋል።
የዕድሉ ተጠቃሚዎችም በቆይታቸው ባገኙት ሥልጠና እና የሥራ ዕድል ከተረጅነት ተላቀው የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋገጥ መጀመራቸውን ተናግረዋል። በተመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታ እና የገንዘብ ድጋፍ በርትተው በመሥራት ለሌሎችም አርዓያ ለመኾን እንደሚሠሩም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡- ሳሙኤል አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!