
ባሕር ዳር: ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የግሪሳ ወፍን ለመከላከል ከ190 ሄክታር በላይ በሚሸፍኑ ዘጠኝ የወፍ ማደሪያዎች ላይ የኬሚካል ርጭት መደረጉን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገልጿል። ተዛማች ድንበር ተሻጋሪ እየተባሉ ከሚጠሩት ተባዮች ውስጥ የግሪሳ ወፍ አንዱ ነው። የአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ችግር ተደርጎም ይወሰዳል።
ሥነ ምሕዳርን መሠረት በማድረግ ምግብ ለማግኘት እና ለመራባት ወደ አመች ቦታ ይጓዛሉ። የክብደታቸውን ያህል በመመገብ በቀን እስከ 64 ኪሎ ሜትር በመጓዝ እና ብዙ ቦታ ላይ በመድረስ ከፍተኛ ጉዳት የማድረስ አቅም አላቸው። በ12 ቀናት ውስጥ እንቁላል በመፈልፈል ሰብልን ለመብላት የሚደርስ ነው። በአብዛኛው ጉዳት የሚያደርሰው ደግሞ በመኸር ወቅት እንደኾነ የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል።
የአማራ ክልል በተለይም ደግሞ የምሥራቁ ክፍል በየጊዜው በበርሃ አንበጣ እና ተዛማች ተባዮች ሲፈተን ተስተውሏል። በዚህ ዓመትም በክልሉ ሦስት ዞኖች በሚገኙ አምስት ወረዳዎች የግሪሳ ወፍ ተከስቷል። ከተከሰተባቸው ወረዳዎች ደግሞ የሰሜን ሽዋ ዞን የቀወት ወረዳ አንዱ ነው። የወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ታስቻለ ጎሽሜ እንዳሉት የግሪሳ ወፍ ከመስከረም 21/2017 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳው አራት ቀበሌዎች የግሪሳ ወፍ ተከስቷል።
ለሰባት ቀናት በወረዳው በተመረጡ ቦታዎች በተደረገው ርጭት መቆጣጠር መቻሉንም ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ከአፋር ተነስቶ ወደ አካባቢው የመምጣት ዕድል ስላለው ከሚመለከታቸው ተቋማት እና ከአርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት የአሰሳ እና ክትትል ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ነግረውናል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የዕጽዋት ጥበቃ ባለሙያ አበበ አናጋው እንዳሉት የግሪሳ ወፍ በክልሉ ሰሜን ሸዋ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በደቡብ ወሎ ዞን በአምስት ወረዳዎች በሚገኙ 13 ቀበሌዎች የግሪሳ ወፍ ተከስቷል። የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ አርሶ አደሮች በባሕላዊ መንገድ ሲከላከሉም እንደቆዩ ተገልጿል።
የተከሰተው የግሪሳ ወፍ ጉዳት ማድረስ ከሚችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ የአውሮፕላን ርጭት ጭምር ማድረግ አስገድዷል ብለዋል። በዚህም በክልሉ ከተለዩት 14 የወፍ ማደሪያ ቦታዎች ውስጥ 190 ነጥብ 5 ሄክታር በሚሸፍኑ ዘጠኝ የወፍ ማደሪያዎች ቦታ ላይ 381 ሊትር የኬሚካል ርጭት ተደርጓል ብለዋል። ኬሚካሉ እስከ 98 በመቶ የግሪሳ ወፍን የመግደል አቅም ያለው በመኾኑ ውጤታማ እንደነበር ነው የገለጹት።
ባለሙያው እንዳሉት የግሪሳ ወፉ በአፋር ክልል በበረሃማው አካባቢ ሊመገበው የሚችለው ሰብል እና ሳር ሲደርቅ የተሻለ ምግብ ለማግኘት ወደ ምሥራቁ የአማራ ክፍል የመንቀሳቀስ ዕድል ስላለው የአሰሳ ሥራ ከተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ማኅበረሰቡ በባሕላዊ መንገድ የመከላከል ሥራውን እንዲያጠናክር እና የደረሱ ሰብሎችን በወቅቱ እንዲሠበሥብም ጥሪ አቅርበዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
