ዩኒቨርስቲው የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሀገር በቀል እውቀት ላይ እየሠራ መኾኑን ገለጸ።

25

ደሴ: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሀገር በቀል የባሕል ሕክምና እና በባሕላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓቶች ላይ ያተኮረ ውይይት አካሂዷል፡፡ በውይይቱ የዩኒቨርስቲው የሥራ ኀላፊዎች፣ የጤና ሚኒስቴር የባሕል ሕክምና ዴስክ አሥተባባሪ ናትናኤል ሰለሞን፣ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎች፣ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው ተገኝተዋል፡፡

በባሕል ሕክምና ላይ በርካታ ጥናትና ምርምሮች ያደረጉት እና በውይይቱ ንግግር ያደረጉት የቀድሞው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አሰፋ ባልቻ (ዶ.ር ) በዘመናዊ እና በባሕላዊ ሕክምና መካከል በሀገራችን ሰፊ ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ክፍተቱን ለመሙላትና የባሕል ሕክምናውን ለማሳደግ በባለቤትነት የሚመራ ተቋም መመስረት እንደሚያስፈልግና ወሎ ዩኒቨርስቲ የጀመረውን ተግባር እንደሚያደንቁ ገልጸዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርስቲ የባሕል፣ ኪነ ጥበባትና ሀገር በቀል ዕውቀት ዳይሬክተርና የፎክሎር መምህር ብርሃን አሰፋ (ዶ.ር) ዩኒቨርስቲው የልህቀት ማዕከል ለመኾን ከሚሠራባቸው አንዱ የሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ እንደኾነ ገልጸዋል። የባሕል ሕክምና አዋቂዎች እያለፉ፤ ዕውቀታቸውም እየጠፋ፣ ለሕክምና የሚውሉ ዕፅዋትም እየተመናመኑ በመኾናቸው የጋራ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

የውይይይቱ ዓላማም በሀገር በቀል ዕውቀቶች ላይ የሚሠሩ ተመራማሪዎችን ከባሕል ሕክምና አዋቂዎችና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በማገናኘት ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ለማፈላለግና ተቀራርቦ ለመሥራት መኾኑን ገልጸዋል፡፡ የጤና ሚኒስቴር የባሕል ሕክምና ዴስክ አሥተባባሪ ናትናኤል ሰለሞን መንግሥት ለባሕል ሕክምና ልዩ ትኩረት መስጠቱን ነው የተናገሩት፡፡ የባሕል ሕክምና ዕውቀት በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ እንዲካተት ጤና ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየሠራ እንደሚገኝም አሳውቀዋል፡፡

በውይይቱ የተገኙ የባሕል ሕክምና አዋቂዎች “ወሎ ዩኒቨርሲቲ ይህንን መሰል ውይይት በማዘጋጀቱ ሊመሠገን ይገባል” ብለዋል። ከዩኒቨርስቲው ጋር በትብብር ለመሥራትና ሀገር በቀል ዕውቀት ዕውቅና ተሰጥቶት በዘመናዊ ትምህርት ሥርዓት ቢካተት ዕውቀታቸውን ለማካፈል ዝግጁ እንደኾኑ ተናግረዋል።
ጤና ሚኒስቴር ለባሕል ሕክምና የሰጠው ትኩረት የሚመሠገን እንደኾነና ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡

የወሎ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ሀዋ ወሌ (ዶ.ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ከባሕል ሕክምና አዋቂዎች ጋር ተቀራርቦ በመሥራት ያሉባቸውን የዕውቅና፣ የቦታና ሌሎች ችግሮች መፍትሔ እንዲያገኙ ለመመካከር አስፈላጊ ውይይት ነው ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ከድር አሊ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የባቡር መንገድ ፕሮጀክቱ አማራ ክልልን በሁሉም ቀጣና ለማስተሳሰር ከፍተኛ ፋይዳ አለው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር )
Next articleየ5ኛ ትውልድ የመረጃ መረብ!