“የባቡር መንገድ ፕሮጀክቱ አማራ ክልልን በሁሉም ቀጣና ለማስተሳሰር ከፍተኛ ፋይዳ አለው” አብዱ ሁሴን (ዶ.ር )

38

ደሴ: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአዋሽ ኮምቦልቻ ሃራ ገበያ የባቡር መንገድ ፕሮጀክት የጥበቃ ጉዳይ እና ቀጣይ ሥራዎችን በተመለከተ በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት ተካሂዷል። ውይይቱን የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር)፣ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አሥተባባሪ እና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው እና የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጂነር ህሊና በላቸው መርተውታል።

በውይይቱ የደቡብ ወሎ፣ የሰሜን ሽዋ ዞን፣ የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር፣ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር፣ የወረዳ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች እና የፀጥታ አካላት ተሳታፊ ናቸው። የውይይቱ ተሳታፊዎች ማኀበረሰቡ የባቡር መንገድ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት ስሜት ጥበቃ እያደረገለት ነው ብለዋል። የጥበቃ ሠራተኞችም ለረጅም ጊዜያት ደመወዝ አልተከፈለንም ሳይሉ ፕሮጀክቱን ለመጠበቅ መስዋትነት እየከፈሉ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ኢንጂነር ህሊና በላቸው ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ከተቋራጩ ጋር ንግግሮች መቀጠላቸውን ገልጸዋል። የፕሮጀክቱ ንብረቶች ጥበቃ እንዲደረግላቸው እየተደረገ ነው ያሉት ሥራ አሥፈፃሚዋ በራስ አቅም የተወሰኑ ማስተካከያዎችን እና ጥገናዎችን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ጉዳዮች አሥተባባሪ እና የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኀላፊ ደሳለኝ ጣሰው የሕዝብ መሠረተ ልማቶችን በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት መዋቅር እና ማኅበረሰቡ ጥበቃ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ በፕሮጀክቶች ሕገወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ የጸጥታ መዋቅሩ እና የፍትሕ አካላት ተገቢውን እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን (ዶ.ር ) የባቡር መንገድ ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን አጠቃላይ የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ አቅም ለማሳደግ ብሎም አማራ ክልልን በሁሉም ቀጣና ለማስተሳሰር ከፍተኛ ፋይዳ አለው ብለዋል፡፡ በፕሮጀክቱ ላይ የሚታዩ አኹናዊ ችግሮችን በባለቤትነት ስሜት በወቅቱ መፍታት ይገባልም ነው ያሉት።

ዘጋቢ ፦አንተነህ ፀጋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአርሶ አደሮች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በሚያከማቹት የምርት ደረሰኝ ብድር እየተመቻቸላቸው መኾኑ ተገለጸ።
Next articleዩኒቨርስቲው የልህቀት ማዕከል ለመሆን የሀገር በቀል እውቀት ላይ እየሠራ መኾኑን ገለጸ።