
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደሮች በመጋዘን በሚያስቀምጡት ምርት በሚሰጣቸው ደረሰኝ ብድር መውሰድ በሚችሉበት ሁኔታ በባሕርዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል። አርሶ አደሮች ያመረቱት ምርት በገበያ ላይ ዋጋው በቀነሰ ወቅት ምርታቸው እንዳይበላሽ ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት መጋዝን ምርታቸውን ያከማቻሉ፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅት ደግሞ አርሶ አደሮች በመጋዝኑ ውስጥ ያስቀመጡትን የምርት መጠን እና ደረጃውን የሚገልጽ ደረሰኝ ለአርሶ አደሮች እና ለኅብረት ሥራ ማኅበራት ይሰጣል፡፡ ይህንን ደረሰኝ አርሶ አደሮች፥ እንደማስያዢያ በማሲያዝ ከባንክ ብድር እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ተብሏል።
ብድር የወሰዱ፥ አርሶ አደሮችም በገበያ ላይ የምርት መሸጫ ዋጋ ሲስተካከል ከተከራዩት መጋዝን ምርታቸውን አውጥተው በመሸጥ ለባንኩ ዕዳቸውን መክፈል እንደሚችሉ ነው የተገለጸው። በዚህ የብድር አገልግሎት አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መኾናቸውም ተመላክቷል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን የኮኪት የገበሬዎች ኅብረት ሥራ ማኅበር ሊቀመንበር አፍራሻ ደምሴ ምርታቸውን ለኢትዮጵያ ምርት ገበያ እያቀረቡ እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ ባለፈው ዓመት የሰሊጥ ምርት ላይ የገበያ መውረድ ገጥሟቸው እንደነበር የተናገሩት ሊቀመንበሩ የሰሊጥ ምርት ገበያ የተሻለ እስኪኾን ድረስ ብር ከባንክ ተበድረው መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ባንክ ደግሞ በቅርበት ችግራቸውን በመረዳት እንዳበደራቸውም ተናግረዋል።
ብድር ከወሰዱ ከ55 ቀናት በኋላ ገበያው ሲመለስ በጥሩ ዋጋ ሸጠው እዳቸውን መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ሊደርስባቸው ከነበረው ኪሳራ ድነው ትርፋማ እንደኾኑም ተናግረዋል፡፡ አማራ ባንክ ብቻ ሳይኾን ሌሎች ባንኮችም ለአርሶ አደሮች ብድር ማመቻቸት ይገባቸዋል ነው ያሉት፡፡ ከኪሳራ ላዳናቸው አማራ ባንክም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡ አርሶ አደሮች ዋጋ በሚቀንስ ጊዜ ብድር እያመቻቹ የተሻለ ዋጋ ሲኖር መሸጥ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች ተጠቃሚ እንዲኾኑ እየተከታተለ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አንስተዋል፡፡
በአማራ ባንክ የባሕርዳር ድስትሪክት የደንበኞች ግንኙነት ሥራ አሥኪያጅ መሪጌታ ነብዩ ኢያሱ ባንኩ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ የብድር አገልግሎት በስፋት እየሠጠ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሮችን ጨምሮ ለተለያዩ አካላት የብድር አገልግሎት እያመቻቸ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡ ግብርናውን ለማዘመን የሚያስችሉ ትራክተሮችን ለክልሉ አርሶ አደሮች ማሰራጨቱንም ተናግረዋል፡፡
በምርታቸው አማካኝነት ብድር በማመቻቸት አርሶ አደሮችን እና ኅብረት ሥራ ማኅበራትን ተጠቃሚ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡ የሚሰጠው ብድር አርሶ አደሮች ምርታቸውን በዝቅተኛ ዋጋ እንዳይሸጡ እንደሚያደርጋቸውም ገልጸዋል፡፡ ለአርሶ አደሮች የሚያቀርቡት ብድር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል፡፡ አርሶ አደሮች የሚጠበቅባቸውን መስፈርት አሟልተው ከመጡ በአጭር ቀናት ብድር እንደሚመቻችላቸውም ገልጸዋል፡፡ የተዘረጋላቸውን የብድር አገልግሎት በመጠቀም ከኪሳራ በመዳን ውጤታማ መኾን እንደሚችሉም አመላክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመጋዝን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ክፍል ኀላፊ ብርሃኑ ጥሩነህ አምራቾች፣ ኅብረት ሥራ ማኅበራት እና አቀናባሪዎች ምርታቸውን አስይዘው የአጭር ጊዜ ብድር መውሰድ እንደሚችሉ ገልጸዋል፡፡ ምርት በስፋት በሚቀርብበት የመኸር ወቅት የምርት ዋጋ እንደሚቀንስ የተናገሩት ኀላፊው አርሶ አደሮች በርካሽ ሸጠው ተጠቃሚ ስለማይኾኑ ምርታቸውን ደረጃውን በጠበቀ መጋዘን አስቀምጠው አቆይተው የተሻለ ዋጋ በሚያገኙበት ጊዜ መሸጥ እንደሚችሉ ነው የተናገሩት፡፡
የብድር አገልግሎቱ የፋይናንስ ተደራሽ ላልኾኑ አርሶ አደሮች ተደራሽ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ የግብይት ሠንሰለቱ ግልጽ እና አጭር እንዲኾን፣ ምርት ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ በመጋዘን እንዲቀመጥ እንደሚደረግም ተናግረዋል፡፡ ምርት ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሲገባ በሕገወጥ መንገድ የሚያዘውን ምርት ማስቀረት እንደሚቻልም አንስተዋል፡፡
የብድር አገልግሎቱ አምራቾችን፣ ኅብረት ሥራ ማኅበራትን እና አቀናባሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮችን በቅርበት ተጠቃሚ ለማድረግም እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ አርሶ አደሮች ግንዛቤ እዲኖራቸው እንሠራለንም ብለዋል፡፡ አርሶ አደሮች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባስቀመጡት ምርት ብድር ከወሰዱ በኋላ የገበያ ችግር እንዳይገጥማቸው ገበያ እንደሚያመቻቹም ገልጸዋል፡፡ የብድር አገልግሎቱ አርሶ አደሮች የበለጠ ተጠቃሚ እንዲኾኑ እና ኑሯቸውን እንዲያሻሽሉ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡
አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡ በብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እየኾኑ ሲሄዱ ምርት እና ምርታማነታቸውን እያሳደጉ እንደሚሄዱም አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!