
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ እየተወሰዱ በሚገኙ ሕግ የማስከበር እርምጃዎች የከተማዋ የሰላም ሁኔታ እየተሻሻለ መምጣቱ ተመላክቷል። የሰለም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊው ጌትነት አናጋው እንዳሉት ክልሉ በተለይ ከነሐሴ 2015 ጀምሮ በገጠመው የሰላም እጦት በከተማዋ ሰፊ ምጣኔ ሐብታዊ፣ ማኀበራዊ እና ፖለቲካዊ ችግሮች ተፈጥረዋል። መንግሥት ችግሮችን ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉንም ተናግረዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ከማኀበራዊ ችግሮች አኳያ ትምህርት ቤቶች እና ጤና ጣቢያዎች እንዲዘጉ እና ሥራ እንዲያቋርጡ ተደርገው ቆይተዋል። ስለኾነም በከተማዋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል ብለዋል። ሆቴሎች እና ሌሎች ማኀበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም በዘራፊው ቡድን ሥራቸውን እንዲያቋርጡ ሲደረግ እንደነበር አብራርተዋል። ይህም በምጣኔ ሐብት ረገድ ከፍተኛ ኪሳራ እንዲደርስ አድርጓል ብለዋል።
ዘራፊው ቡድን መንገዶችን በመዝጋት እና የንግዱ ማኀበረሰብ ከቀየው ለቅቆ እንዲሰደድ አድርጓል ብለዋል። በተለይ ስልክ እየተደወለ ገንዘብ እንዲከፍሉ በማስፈራራት አልከፍልም ያለን ባለሐብት እንዲታገት፣ ንብረቱ እንዲቀማ ከፍ ሲልም ጥቃት ይፈጸም እንደነበር ገልጸዋል። በባሕር ዳር የነበረው የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንዲቆም ተደርጎ እንደነበር ያስታወሱት ኃላፊው በዚህ ምክንያት የምጣኔ ሐብት ቀውስ መፈጠሩንም ተናግረዋል።
ዘራፊው እና የጥፋት ቡድኑ በባሕር ዳር ከተማ ካደረሰው ጥፋት እንደ ማሳያ በግዮን አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመማር ማስተማር ላይ የነበሩ ተማሪዎችን እና መምህራንን በፈንጅ እና ቦምብ ፍንዳታ ግድያ ፈጽሟል፤ ሕጻናትን አቁስሏል ብለዋል አቶ ጌትነት። በጣና ሐይቅ እና በባሕር አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ምንም የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸውን ተማሪዎች በፈንጅ እና ቦምብ ፍንዳታ የማሸበር ተግባር ፈጽሟል ነው ያሉት መምሪያ ኃላፊው።
ዘራፊው ቡድን የአንድን ቤተሰብ አምስት አባላት ገንዘብ ጠይቆ አንከፍልም በማለታቸው በአሰቃቂ ኹኔታ ግድያ ፈጽሞባቸዋል ነው ያሉት። የሃይማኖት አባቶችም ይታገቱ ነበር ያሉት የሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊው በድርድር ገንዘብ እንዲከፍሉ ይደረግ ነበር ብለዋል። ዘራፊ እና አጋቹ ቡድን የሕዝብን ሰላም በመቀማት የጽንፈኛነት ተግባሩን በከተማዋ ውስጥ ሲያራምድ ቆይቷል። ፍላጎቱን በማኀበረሰቡ ላይ ለመጫንም ሰፊ ጥረት ያደረግ ነበር ብለዋል አቶ ጌትነት በሰጡት መግለጫ።
ችግሩን ለመፍታትም የከተማ አሥተዳደሩ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ተነጋግሮ በመግባባት ሰፊ ሥራ መከናወኑን አቶ ጌትነት ተናግረዋል። አሁን ላይ በባሕር ዳር እና በዙሪያዋ አንጻራዊ ሰላም ማስፈን ተችሏል ያሉት ኃላፊው የጸጥታ ኃይሉ በወሰደው እርምጃም 1 መቶ 21 አጋቾችን እና ዘራፊዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ለሕግ ቀርበዋል ብለዋል። በመኾኑም ማኀበረሰቡ እፎይታ አግኝቷል፤ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ተከፍተው ወደ ሥራ ገብተዋል ብለዋል አቶ ጌትነት።
ከባሕር ዳር ባለፈ በዘጌ፣ መሸንቲ እና ጢስ ዓባይ ከተሞችም አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ የመማር ማስተማር እና የሕክምና አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛሉ ነው ያሉት። የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው በበኩላቸው በከተማዋ የነበረው የጸጥታ መደፍረስን ለማጥራት ሰፊ ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
ኮማንደር ዋለልኝ አክለውም በከተማዋ የፖሊስ አገልግሎትን ቀበሌ ድረስ ተደራሽ በማድረግ እንደ ትምህርት ሁሉ ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶችም መልሰው ሥራ እንዲጀምሩ ተደርገዋል ነው ያሉት። ሕዝቡም ከፖሊስ ጋር በመሥራቱ በውስጥ እና በውጭ ከጥፋት ቡድኑ ጋር ይሠሩ የነበሩ አደገኛ ወንጀለኞችን መያዝ ተችሏል ብለዋል ኮማንደሩ።
በከተማዋ ሁለት ዓይነት እገታ ነበር ያሉት ኮማንደር ዋለልኝ የመጀመሪያው ገንዘብ ፍለጋ ሲኾን ሁለተኛው ከጽንፈኛው ቡድን ጋር በመነጋገር ማኀበረሰቡን ረፍት ለመንሳት ያለመ ነው። በመኾኑም የጸጥታ ኃይሉ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራው ተጣርቶ ለሚመለከተው ክፍል ተላልፏል ነው ያሉት።
በዚህ ሳምንት ብቻ በዘራፊዎች ተወስደው የነበሩ ከ10 በላይ የመንግሥት እና የግለሰብ መኪናዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል። አሁን ሁሉም መንገዶች ክፍት እንዲኾኑ መሠራቱን ኮማንደሩ ጠቅሰዋል። “በከተማዋ አሁን ላይ የልማት ሥራዎችን ለማከናዎን ሥጋት የሚኾን ነገር የለም። ባሕር ዳር ከምንም ነገር ነጻ ኾና ማንኛውንም ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች የሚከናወንባት ከተማ መድረግ ተችሏል” ብለዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!