“ኅብረተሰቡን በቀናነት በማገልገል ችግሮችን ለመፍታት መነሳሳት ያስፈልጋል” የመንግሥት ሠራተኞች

33

ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳድር ”የህልም ጉልበት ለእምርታዊ እድገት” በሚል መሪ ቃል በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለብልጽግና ፓርቲ አባል የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና እየሰጠ ነው። በሰላም፣ በልማት፣ በአገልግሎት አሰጣጥ እና በመልካም አሥተዳደር ጉዳዮች ላይ የሠራተኞች ሚናን በማሳደግ የኅብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስ እና ርካታውን ለማሳደግ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ ነው ውይይት የሚደረገው።

በባሕር ዳር ከተማ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ፈጣን ምላሽ ባለሙያ ጢሞቴዎስ ኦርዴንቶ በወቅታዊ የሰላም፣ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት አጀንዳዎች ላይ ውይይት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል። ሀገራዊ አጀንዳዎችን በተለይም የሰላም ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል እና የመንግሥት ሠራተኛውም ድርሻ ከፍተኛ እንደኾነ ግንዛቤ መያዙን ገልጸዋል። ለመልካም አሥተዳደር ችግር መፈታትም የመንግሥት ሠራተኞች ድርሻን ከፍተኛነት በመገንዘብ ያለውን ችግር በውጤታማ መንገድ ለመፍታት ነው ውይይት እያደረግን ያለነው ብለዋል።

ሰላምን በማስፈን በኩልም ኅብረተሰቡ ያለውን የሰላም ፍላጎት በመገንዘብ ለሰላም በጥንካሬ መሥራት እንደሚጠበቅ ግንዛቤ መያዙን ነው የገለጹት። በባሕር ዳር ከተማ ሴቶች፣ ህጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የአቅም ግንባታ ባለሙያ ትክክል ማኅተም በበኩላቸው በሚሰጠው ሥልጠና የባሕር ዳር ከተማን የአገልግሎት አሰጣጥ እና የሰላም ችግሮች ለመፍታት የሚያስችል ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

የሰላምም ኾነ የአገልግሎት አሰጣጡ ችግር በገጠመው ጊዜ አካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን የበለጠ ተጎጂ ናቸው ያሉት ወይዘሮ ትክክል በቀጣይ አገልግሎት አሰጣጣቸውን በማሳደግ የሰላም ችግሮችን ለመፍታት በሚደረገው ሥራ የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል። ለተፈጠረው የሰላም ችግር መፈታት የአገልግሎት አሰጣጡን፣ የመልካም አሥተዳደር ችግሮች ለመፍታት መነሳሳት መፈጠሩን ነው የገለጹት።

የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ፖለቲካ እና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኀላፊ ጊዜው ታከለ የሚሰጠው ሥልጠና ለመንግሥት ሠራተኞች እና የገጠር የብልጽግና አባላት እንዲኹም ለአንቀሳቃሾች መኾኑን ገልጸዋል። በየደረጃው የሚገኘው መሪ እና አባላት በፖሊሲ እና ፕሮግራሞች ላይ ግልጽነት መፍጠር፣ በአፈጻጸም ሂደት በታዩ ክፍተቶች ላይ ትምህርት መስጠት፣ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ባጋጠሙ ችግሮች ላይ ግልጽነት ፈጥሮ ሁሉም ኀላፊነትን እንዲወጣ ማስቻል፣ የተሠሩ ፖለቲካዊ፣ የምጣኔ ሃብት እና ማኅበራዊ ሥራዎችን ለማጠናከር መኾኑን ጠቅሰዋል።

አቶ ጊዜው የሥልጠናው ተሳታፊዎችም የተሻለ ግንዛቤ ኖሯቸው የሰላም እጦት፣ የኑሮ ውድነት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታት ሚናቸውን መወጣት እንዲችሉ ግንዛቤ እና መነሳሳት ተፈጥሯል ነው ያሉት። በቀጣይም ለመንግሥት ሠራተኛው ተመሳሳይ ሥልጠና እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበአረንጓዴ ዓሻራ መርሃ ግብር ሥራዎች አማካኝነት በዘላቂ የግብርና ሥራ የታየው የኢትዮጵያ ርምጃ በጉባኤው መቅረቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ገለጹ።
Next articleበባሕር ዳር ከተማ የጸጥታ ኃይሉ እና ሕዝቡ ተቀናጅተው በመሥራታቸው የከተማዋ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን የከተማዋ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ገለጸ።