ከሕግ ማስከበር በተጓዳኝ የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይባክኑ ሰብልን በመሠብሠብ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ ሠራዊቱ ዝግጁ ስለመኾኑ ብርጋዴል ጄኔራል አዘዘው መኮንን ገለጹ፡፡

96

ደብረ ማርቆስ: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሕግ በማስከበር ላይ የሚገኘው በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ403ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል አዘዘው መኮንን በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት አርሶ አደሮች ከምርት ሥራቸው እንዳይነጠሉ እና የምርት ማሳደጊያ ግብዓት ወደ አርሶ አደሮች እንዲደርስ በማድረግ ሠራዊቱ የነበረው ሚና ከፍተኛ ነበር ብለዋል።

የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ሳይበግራቸው አርሶ አደሮች አርሰው በስፋት አምርተው በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ውጤት መገኘት ሠራዊቱ የከፈለው ዋጋ ከፍተኛ እንደነበርም አስታውሰዋል። ብርጋዴል ጄኔራል አዘዘው ከሕዝቡ ጋር በተደረጉ ተከታታይ ውይይቶች ሕዝቡ ለሰላም ያለው ፍላጎት ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል። ጊዜውን እና ጉልበቱን በምርት ሥራው ላይ ማሳለፍ እንደሚፈልግ መግለጹን አስረድተዋል። ሠራዊቱም የሕዝቡን የሰላም ፍላጎት ለማሳካት በትጋት እየሠራ ነው ብለዋል።

የመከላከያ ሠራዊቱ ከሕግ ማስከበር በተጓዳኝ ማኅበረሰቡን በመደገፍ ማኅበራዊ ኀላፊነቱን እየተወጣ እንደኾነም ጠቁመዋል፡፡ የ403ኛ ኮር ዋና አዛዥ ብርጋዴል ጀኔራል አዘዘው የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይባከኑ ሠራዊቱ አርሶ አደሮችን ለመደገፍም ዝግጁ ነው ብለዋል።

በሕዝቡ እና በፀጥታ ኀይሎች ቅንጅት የታየው አንፃራዊ ሰላም ዘላቂነቱ እንዲረጋገጥ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዓለም ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን መገንባት እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ተናገሩ።
Next article“ማኅበረሰቡን በተሻለ አቅም ለማገልገል ዝግጁ ነን” ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ የብልጽግና ፓርቲ አባላት እና መሪዎች