
አዲስ አበባ: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአዲስ አበባ በተካሄደው ከርሀብ ነጻ ዓለም ዓለም ጉባኤ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) በዓለም ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ግብርናን መገንባት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል የግብርና ሥርዓት በመዘርጋት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ወሳኝ መፍትሔ መኾኑን አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያሳድረውን ጫና ለመቋቋም እና ምርታማነትን ለማሳደግ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ተግባራዊ እያደረገች መኾኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ሀገሪቱ ረሀብን ለመቀነስ የሴት አርሶ አደሮች ቁጥር ለመጨመር እና ለመደገፍ የግብርና ፖሊሲዎችን ቀርጻ ወደ ሥራ መግባቷን ተናግረዋል።
ከርሀብ ነጻ ዓለም ለመፍጠር እና በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በትብብር እና በቅንጅት መሥራት እንዳለበትም አስረድተዋል።
በጉባዔው የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ፣ የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ሞኒክ ናሳናባንጋዋ ተሳትፈዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!