“የጋራ ደኅንነት ላይ አተኩሮ በመሥራት እና ተግባራዊ ጥንቃቄም በማድረግ ባንኩ ተጨባጭ እና ለውጥ ያመጡ ሥራዎችን እየሠራ ነው” አቤ ሳኖ

27

አዲስ አበባ: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓለም አቀፉን የመረጃ ሥርዓት ቀን ምክንያት በማድረግ ደኅንነቱ የተጠበቀ የባንክ ሥርዓትን ለማስቀጠል ከብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ምክክር እያካሄደ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን የሳይበር ደኅንነት ብቃት ከፍ ለማድረግ እና ለማጽናት በትብብር መሥራት ያለመ የውይይት መድረክ ነው እየተካሄደ የሚገኘው።

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ የሳይበር ደኅንነት የህልውና ጉዳይ በመኾኑ ሁሉም ራሱን ከሳይበር ጥቃት እንዲጠብቅ አሳስበዋል፡፡ ሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው በሚገባ የተመራ እና ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሁም ከአጭበርባሪዎች የፀዳ መኾን እንደሚገባውም ነው ያብራሩት፡፡

ሀገራት የዜጎቻቸውን ብሎም የተቋሞቻቸውን የሳይበር ደኅንነት ንቃተ ኅሊና ለማሳደግ የሚያስችል የሳይበር ደኅንነት የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብሮችን በማዘጋጀት እንደሚያከብሩ ነው የገለጹት፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ ተቋማቸው ውስጣዊ አቅሙን በማጠናከር ለሥራውም ተገቢ የኾኑ ባለሙያዎችን በማሠልጠን ግብዓቶችን በማሟላት እየሠራ መኾኑን ነው ያስረዱት፡፡

የጋራ ደኅንነት ላይ አተኩሮ በመሥራት እና ተግባራዊ ጥንቃቄም በማድረግ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጨባጭ እና ለውጥ ያመጡ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛልም ብለዋል፡፡ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ዮዳሄ አረዓያ ሥላሴ ኢትዮጵያ የሳይበር ደኅንነት ወርን ስታከብር የተቋማትን የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ ንቅናቄዎችን በማድረግ እንደኾነ አስገንዝበዋል፡፡

የሳይበር ደኅንነት ዘርፍ ላይም የግሉን ዘርፍ ሚና ለማሳደግ እና ለማበረታታት ብሎም በቂ እና ጥራት ያለው የሳይበር ደኅንነት ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር እየተሠራ ስለመኾኑም ተናግረዋል፡፡ የዜጎችን የሳይበር ደኅንነት ግንዛቤ በከፍተኛ ደረጃ ለሕዝብ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን ለመተግበር እና በዲጂታል የአሠራር ሥርዓት የመሠረተ ልማት ደኅንነትን ለማረጋገጥ እንደኾነ ምክትል ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የሳይበር ደኅንነት ወርን ኢትዮጵያ የቁልፍ መሠረተ ልማት ደኅንነት ለዲጂታል ሉዓላዊነት በሚል መሪ መልዕክት ለ5ኛ ጊዜ እያከበረች ትገኛለች፡፡

ዘጋቢ :- ሰለሞን አሰፌ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሠራ መኾኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
Next article“ብልፅግና ፓርቲ እጅግ በበዙ ውስብስብና እልህ አስጨራሽ ፈተናዎች የታጀበ የትግል፣ የተግዳሮትና የለውጥ ዓመታትን ያሳለፈ ፓርቲ ነው” አቶ ይርጋ ሲሳይ