“ለውጥ ማስመዝገብ ከተፈለገ ቁርጠኛ ልብ እና ሥራን ሳይንቁ መሥራት ያስፈልጋል” በዶሮ እርባታ የተሰማሩ እናት

41

ሰቆጣ: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ወጣት ፀሐይ ቸኮለ ትባላለች። በአካውንቲንግ ትምህርት በዲግሪ መርሐግብር ከሦስት ዓመት በፊት ያጠናቀቀች ሲኾን ባለፉት ዓመታት ሥራ ለመፈለግ ከቦታ ቦታ ስትንከራተት መቆየቷን አጫውታናለች። ከስምንት ወር በፊት መንግሥት ያመቻቸላትን ብድር በመጠቀም በ50 ዶሮዎች ሥራዋን መጀመሯን ገልጻለች። አሁን ላይ ብድሯን በመመለስ በቀን ከ35 እስከ 40 እንቁላል ለገበያ ታቀርባለች። ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር የቁጠባ ባሕሏን በማሳደግ የተሻለ ለውጥ ላይ እንደኾነች ነው የነገረችን። በቀጣይም የዶሮ እርባታውን በማሳደግ ለሌሎች ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር መዘጋጀቷን ገልጻለች።

ወይዘሮ ፈትለ አየለ ከፀሐይ ጋር በመደራጀት በዶሮ እርባታ ዘርፍ ተሰማርተዋል። ቤተሰቦቻቸውን የሚያሥተዳድሩት በዚኹ እንደኾነ ነው የሚናገሩት። “ሥራን አለመናቅ የመለወጥ ቁልፍ ነው፤ ለውጥ ማስመዝገብ ከተፈለገ ቁርጠኛ ልብ እና ሥራን ሳይንቁ መሥራት ያስፈልጋል ይላሉ። በሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል የማኅበራዊ ምጣኔ ሃብት ተመራማሪ አደመ ምሕረቱ ማዕከላቸው ቆላማ አካባቢዎችን መሰረት አድርጎ በአምስት ዘርፎች ምርምሮችን እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ማዕከሉ ከአጋዥ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ከ1 ሺህ በላይ ዶሮዎችን ለሃያ እናቶች በብድር መልክ በማከፋፈል የማላመድና ልምድ እያካፈሉ እንደኾነም ጠቁመዋል። ማዕከሉ የዶሮ እርባታ ዘርፉን ከጀመረ ገና ስምንት ወሩ ቢኾንም የተገኘው ለውጥ ግን አበረታች ነው ብለዋል ተመራማሪው። በቀጣይም በርካታ እናቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንሠራለን ነው ያሉት።

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ከ19 ሺህ በላይ ሴቶች በእንስሳትና እንስሳት ተዋጽዖ ዘርፎች የተሰማሩ መኾኑን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ሲሳይ አያሌው ገልጸዋል። እናቶች በዶሮ እርባታ ዘርፍ መሰማራታቸው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትታቸውን ከማሳደግ ባለፈ በአካባቢው የሚከሰተውን የመቀጨጭ ችግርን ለመከላከል የሚያግዝ እንደኾነ ነው የተናገሩት። በቀጣይም ከአጋር ድርጅቶች እና ተቋማት ጋር በመነጋገር በዘርፉ ለሚሠማሩ ሴቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም ኀላፊው ገልጸዋል።

ለዘርፉ ትኩረት በመሰጠቱም ከመንግሥት ተቋማት ባለፈ ሌሎች ተቋማትም እየተሳትፉ ነው። “ራይስ ኤፍኤስ” የተባለ መንግሥታዊ ያልኾነ ድርጅት አስተባባሪ የኾኑት አንተነህ መኩሪያ ድርጅታቸው በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በዝቋላ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች ለሃያ እናቶች ለእያንዳንዳቸው 50 ዶሮዎችን በማከፋፈል የተጀመረው ተግባር አበረታች ለውጥ እያመጣ እንደኾነም ተናግረዋል።

ከሰቆጣ ዝናብ አጠር የግብርና ምርምር ማዕከል ጋር በመተባበር መሰል ድጋፎችን በማድረግ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ድርጅቱ እንደሚሠራም ጠቅሰዋል። በዝቋላ ወረዳ ጽጽቃ ከተማ በዶሮ እርባታ ዘርፍ ውጤታማ የኾኑ እናቶች ያሉበት ደረጃ በባለድርሻ አካላት ተጎብኝቷል። በጉብኝት መርሐግብሩም የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች፣ የረጂ ድረጅቶች መሪዎችና ተወካዮች፣ የዝቋላ ወረዳ አመራሮች፣ የምርምር ተቋሙ የሥራ ኀላፊዎች እና ልምድ ልውውጥ ለመውሰድ የተጠሩ እናቶች ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኮንትሮባንድ ንግድን እና በሙስና ከሀገር የሚሸሽ ገንዘብን ለመከላከል በትብብር ለመሥራት ስምምነት ተደረገ።
Next articleከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት እየተሠራ መኾኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።