
ባሕር ዳር: ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል ጽሕፈት ቤት ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት ገልጻለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አዲስ ከተሾሙት የተመድ የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አሺታ ሚታል ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ስጋት የደቀነውን የሕገ ወጥ የሰዎች፣ የአደገኛ ዕፅ፣ የሐሰተኛ መድኃኒት እንዲኹም የሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል በትብብር ለመሥራት ተስማምተዋል። በተጨማሪም የኮንትሮባንድ ንግድን እና በሙስና ከሀገር የሚሸሽ ገንዘብን በመከላከል ረገድ በትብብር ለመሥራት ስምምነት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።
አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ እነዚህን ጨምሮ ለቀጣናው ስጋት የሚደቅኑ ወንጀሎችን ለመከላከል ከተመድ የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል ጽሕፈት ቤት ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ቁርጠኝነት ማረጋገጣቸውን ኤፍቢሲ ዘግቧል።
አሺታ ሚታል ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እና በቅንጅት መሥራት በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ችግሩን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ እንደኾነ ተናግረዋል። ጽሕፈት ቤታቸው ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ እና የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!