ለመልሶ ልማት ሥራዎች እና ለሰው ተኮር ፕሮጄክቶች ትኩረት መሰጠቱን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ::

83

ደሴ: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር የሚገኙ የልማት ሥራዎችን ጎብኝተዋል። የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ የኾኑት ወይዘሮ አሚናት ይመር ባለቤታቸው በሰሜኑ ጦርነት ተሰውተዋል። የትዳር አጋራቸውን በማጣታቸውም ልጆቻቸውን ለማሥተዳደር ችግር ገጥሟቸዋል። ግለሰቧ በተለይም በመኖሪያ ቤት ችግር ተፈትነውም ነበር።

የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ሰኔ 26/2016 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ በኮምቦልቻ ከተማ ባስጀመሩበት ወቅት የወይዘሮዋን ቤት አንድ ባለሃብት ገንብተው ለማስረከብ ቃል ገብተው ነበር። ባለሃብቱ በገቡት ቃል መሰረትም ዛሬ ግንባታው ተጠናቅቆ ርእሰ መሥተዳድሩ በተገኙበት ርክክብ ተደርጓል፡፡

ወይዘሮ አሚናት ባለቤታቸው ለሀገር በከፈሉት መሥዋእትነት ሕዝብ እና መንግሥት በሰጣቸው ትኩረት መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ልጆቻቸው የበጎነት ልምድን እንዲያዳብሩ እንደሚረዳቸውም ነው የገለጹት፡፡ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ወንደሰን ልሳነወርቅ በከተማ አሥተዳደሩ ለ42 አቅመ ደካሞች የሚኾን ቤት በመገንባት ላይ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ባለሃብቶችና ሌሎች ግለሰቦች የበጎ ሥራዎች ላይ እንዲተባበሩም ምክትል ከንቲባው ጠይቀዋል፡፡

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ለሰው ተኮር ፕሮጄክቶች ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል። በዚህም ለአቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ የዜጎችን ኑሮ ማሻሻልና መልሶ ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል። በዚህም በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠሩ ተግባራት ውጤት ማምጣት ተችሏል ነው ያሉት።

መንግሥት እና ሕዝብ የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ያላቸው ቁርጠኝነት የሚደነቅ ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። ይህ በጎ ተግባርም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ዘጋቢ፦ ደጀን አምባቸው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየጊኒው ጠቅላይ ሚኒስትር አማዲ ኡሪ ባህ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን ጎበኙ።
Next article“ማኅበረሰቡ ጥያቄዎች ሁሉ በሰላም እንዲፈቱ ጽኑ አቋሙን አሳይቶናል” የሰሜን ሸዋ ዞን አሥተዳዳሪ መካሻ ዓለማየሁ