
ከሚሴ: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም በዘላቂነት በማጽናት በሙሉ አቅም ወደ ልማት መግባት እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ አሳስበዋል።
በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር በባቲ ከተማ በወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ዙሪያ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል። በውይይት መድረኩ የክልልና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሥራ ኀላፊዎች፣ የመከላከያ ሠራዊት መኮንኖች እና ከባቲ ከተማና አካባቢዋ የተውጣጡ የኅብረተሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን ለመፍታት ዘርፈ ብዙ ሥራ እየሠራ መኾኑን ገልጸዋል።
በባቲና አካባቢው የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማጽናት ሁሉም በጋራ በመቆም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል። በአንድነት በመቆም እና ለሰላም በመሥራት ግጭትን ማስቆም እና ወደ ልማት መግባት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የባቲ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አብዱ አሕመድ በከተማው ሕዝብን ያሳተፈ የሰላም ግንባታ ሥራ በመሠራቱ አንፃራዊ ሰላም እንዲኖር አስችሏል ብለዋል። የተገኘው አንፃራዊ ሰላም ወደዘላቂ ሰላም ተሸጋግሮ በተሟላ መንገድ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎች እንዲፈቱ ታጥቀው በጫካ የሚንቀሳቀሱ አካላት በሰላም ካውንስል በኩል የቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ወደ ቀያቸው ሊመለሱ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።
በመድረኩ የተሳተፉ የባቲ ከተማ ነዋሪዎች ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት መኾኑን ገልጸው የአካባቢያቸውን ሰላም ለማረጋገጥ ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እየሠራን ነው፤ እንሠራለንም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!