
ደብረ ማርቆስ: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከአሜሪካ መንግሥት በሚገኝ ድጋፍ እና በመንግሥት በሚደጎም የገንዘብ ምንጭ የምግም ዋስትና እና ሴፍቲኔት ተጠቃሚ ከኾኑ ከተሞች ውስጥ ደብረ ማርቆስ ከተማ አንዷ ናት። በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ዜጎችን በዚሁ የምግብ ዋስትናና ሴፍቲኔት መርሐ ግብር በማካተት ተጠቃሚ ማድረጉን የከተማ አሥተዳደሩ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ማሥተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።
ጽሕፈት ቤቱ በሁለት ዓመት ውስጥ ከ1ሺ 9መቶ በላይ እማወራ እና አባወራዎችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች በማሰማራት የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ እየሠራ ነው። የከተማ ሴፍቲኔት የከተሞችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ የሥራ ባሕልን የሚያዳብር እና ቁጠባን የሚያለማምድ ተግባር ነው፡፡ በከተማ አሥተዳደሩ በዝቅተኛ ገቢ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን በጥናት በመለየት በከተማ ጽዳት እና ውበት፣ በከተማ ግብርና፣ በተቀናጀ የተፋሰስ ልማት እና በሌሎች ገቢ ማስገኛ ሥራዎቸ ማሰማራት ተችሏል፡፡
በዚህ መርሐ ግብር ከ7 ሺህ በላይ ቤተሰቦች ተጠቃሚ ማድረግ እንደተቻለ የከተማ አሥተዳደሩ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ማሥተባበሪያ ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አየሁዓለም አድማሱ ተናግረዋል። ዜጎች መሥራት የሚችሉበትን የሥራ መስክ እንዲመርጡ እድል በመስጠት በሥልጠና የታገዘ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ድጋፍ እየተሰጠ ነውም ብለዋል።
በደብረ ማርቆስ ከተማ በመርሐ ግብሩ የተካተቱ ዜጎች ከ40 ሄክታር በላይ መሬት የሰብል ምርት በመስኖና በመኸር ወቅት እንዲያለሙ በማድረግ ከራሳቸው ባለፈ ለገበያ እያቀረቡ መኾኑን ኀላፊዋ ገልጸዋል። ዜጎች ከተረጅነት እንዲወጡ እና በቋሚ የሥራ ዘርፍ እንዲሰማሩ የሚያስችል የሙያ ሥልጠናም እየተሠጠ እንደሚገኝ ኀላፊዋ ተናግረዋል። የሥራ ቦታ እንዲመቻች እና የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳኾኑም ጠይቀዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!