
ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከፍተኛ ሃብት ያስመዘገቡ ባለሃብቶችን ፈቃድ በመስጠት ወደ ሥራ እንዲገቡ ማድረጉን የሰሜን ወሎ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ አስታውቋል፡፡ ሰሜን ወሎ ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ የተጎዳ በመኾኑ በኢኮኖሚ እንዲያገግም የኢንቨስትመንት ቦርዱ በትኩረት እየሠራ መኾኑን የሰሜን ወሎ ዞን ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሞላ ደሱ ተናግረዋል፡፡
ሀገሪቱ ካሰበችው እና ከአቀደችው ዕቅድ ለመድረስ ክልሉ ለኢንቨስትመንት ዘርፉ በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም የሰሜን ወሎ ዞን ከሰሜኑ ጦርነት ጀምሮ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ስጋት የፈጠረ ቢኾንም ይህን በመቋቋም 55 ባለሀብቶች 17 ቢሊዮን ብር በማስመዝገብ ወደ ልማት የገቡ መኾኑን ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
በሰሜን ወሎ ዞን ባለሃብቱ ገብቶ እንዲያለማ አሠራርን ፍትሐዊ ለማድረግ፣ ከአጋር አካላቶች ጋር ለመነጋገር እና የፋይናንስ አገልግሎት አሰጣጥን ምቹ ለማድረግ የኢንቨስትመንት ቦርዱ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በተያዘው ሩብ ዓመትም ወደ 334 ለሚኾኑ የሥራ ፈላጊ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠሩ መኾናቸውንም ነው ያብራሩት፡፡
ባለሃብቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር እና ከልማት ሥራው በተጨማሪ በሩብ ዓመቱ የተቸገሩ ተማሪዎችን ለመርዳት 156 ሺህ ብር ድጋፍ ማድረጋቸውም ተጠቁሟል፡፡ ዞኑ ካለው እምቅ ሀብት አንጻር ሲታይ አሁን ያለው የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም ያሉት ኀላፊው በቀጣይ ባለሀብቶች ያላቸውን መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ ወደ ልማት እንዲገቡ አስተማማኝ ሰላም መፍጠር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡ ለዚህም መንግሥት ሰላምን ማስጠበቅ ይኖርበታል ነው ያሉት፡፡
ኀላፊው በከተማም በገጠርም የመሬት አቅርቦት ፋይናንስን በመጠቀም ለኢንዱስትሪ የሚኾኑ ቦታዎችን የማዘጋጀት ሥራ መሠራቱን ተናግረዋል፡፡ ባለሀብቱም ያለውን ሃብት ኢንቨስት በማድረግ አካባቢውን እንዲያለማ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!