
አዲስ አበባ: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) 300 የሚኾኑ ቀጣሪ ድርጅቶች በተገኙበት ከ30 ሺህ በላይ የሥራ ዕድሎችን የሚፈጥረው አምስተኛው ሀገር አቀፍ የሥራ አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል። አውደ ርዕዩ የተዘጋጀው በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር፣ በደረጃ ዶት ኮም እና በማስተር ካርድ ፋውዴሽን ትብብር ነው።
ይህ የሥራ አውደ ርዕይ ለሁለት ቀን የሚቆይ ሲኾን ከ20 ሺህ በላይ የደረጃ ክህሎት ሥልጠና የወሰዱ የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን ከ300 በላይ ከተለያየ ዘርፍ ከተወጣጡ የሥራ ቀጣሪዎች ጋር የሚተዋወቁበት እንደኾነ የማስተር ካርድ ፋውዴሽን ዳይሬክተር ኤልያስ ያለው ተናግረዋል። የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሰለሞን ሶካ የኢትዮጵያ የሰው ኀይል በዓለም ተወዳዳሪ እንዲኾን ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑ አስገንዝበዋል፡፡
ሚኒስትሩ የሰው ኀይሉ የሠለጠነ እና ሙያውን በአግባቡ ያወቀ እንዲኾን መንግሥት ከሚመለከታቸው አጋር አካላት ጋር እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩም አመራጮችን በማስፋት ላይ እንደሚገኙም ገልጸዋል። በቀጣይ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ከትምህርት ተቋማት ጋር በመተባበር ለዜጎች የክህሎት ማበልፀጊያ ሥልጠናዎችን ለመስጠት ዕቅድ መያዙን አቶ ሰለሞን ጠቅሰው በክህሎት የበለፀገ ዜጋ ለመፍጠር ሁሉም ትብብር ሊያደርግ ይገባል ብለዋል
ዘጋቢ፡- ራሔል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!