“ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቅንጅት መሥራት ከቻለ ድህነትን ታሪክ ማድረግ ይቻላል” መላኩ አለበል

77

አዲስ አበባ: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከርሃብ ነጻ የኾነ ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ በአዲስ አበባ የአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው። በጉባኤው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል፣ የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል ገርድ ሙለርን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ምሁራን እና የቴክኖሎጂ አቅራቢዎች እየተሳተፉ ነው።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል ኢትዮጵያ የዜጎቿን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በኢንዱስትሪ እና በግብርናው ዘርፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ነው ብለዋል። በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማቋቋም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር በጋራ እንደምትሠራም አስረድተዋል።

ከርሃብ ነጻ የኾነ ዓለም መፍጠር የሚቻለው ዓለማም አቀፉ ማኅበረሰብ በሁለንተናዊ ዘርፎች በቅንጅት እና በትብብር መሥራት ሲችል ነው ብለዋል። ሁለንተናዊ ትብብር እና ቅንጅት ካለ ርሃብ ታሪክ የማይኾንበት ምክንያት የለም ነው ያሉት። የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ገርድ ሙለር የአየር ንብረት ለውጥ እና በዓለም የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ ችግር ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለከፋ ችግር እና እንግልት እየዳረገ መኾኑን አንስተዋል።

ርሃብ እና ድህነትን ለመቀነስ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ እና በኢንቨስትመንት ዘርፉ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቅንጅት መሥራቱ ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል። በተለይም የመንግሥት እና የግል ኢንቨስትመንት ዘርፉን ማነቃቃት እና የውጭ ቀጥታ ንግድን ማሳደግ እንደሚገባም ነው የተናገሩት። ግብርናን በቴክኖሎጅ መደገፍ እና ኢንዱስትሪን ከቴክኖሎጅ እና ኢንቨስትመንት ጋር በማስተሳሰር መሥራት ወሳኝ እንደኾነም አብራርተዋል።

ይህ ከርሃብ ነጻ ዓለም የመፍጠር ዓለም አቀፋዊ ጉባኤ የዓለምን የምግብ ዋስትና ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማስቀመጥ የሚያስችል ወሳኝ ጉባኤ ነው ብለዋል።

ዓለምን እየተገዳደረ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ እና የርሃብ አሳሳቢነት ችግርን ከምንጩ ለመፍታት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምን ማድረግ እንዳለበት በጋራ ለመወያየት እና ዘላቂ መፍትሔ ለማስቀመጥ የሚጠቅም ጉባኤ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበክልል ደረጃ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቱን ለማሻሻል እና የሚጠበቅበት ደረጃ ላይ ለማድረስ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
Next article20 ሺህ ለሚኾኑ አዲስ ምሩቃን የሥራ ዕድልን የሚፈጥር አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ተከፈተ።