
ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በክልል ደረጃ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቱን ለማሻሻል እና የሚጠበቅበት ደረጃ ላይ ለማድረስ እየሠራ መኾኑን የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቤል ፈለቀ በክልሉ በአራት መሠረታዊ ፕሮግራሞች ላይ በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ማኅበረሰብ እና ተቋም አቀፍ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የንቃተ ኅሊና ፕሮግራሞችን ማሻሻል የመጀመሪያው መኾኑን ገልጸዋል፡፡ ቴክኖሎጂ ላይ መሠረት ያደረገ በተቋም እና በማኅበረሰብ ያለውን የግንዛቤ ደረጃ ከፍ በማድረግ ወቅቱን እንዲመጥን የማድረግ ሥራ መሠረታዊ ጉዳይ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡
የዲጂታላይዜሽን ግንዛቤን ካሳደግን በኋላ ቴክኖሎጂን የሚጠቀም ማኅበረሰብ እንዲኖር የመሠረተ ልማት ማሻሻያ ማድረግ ሁለተኛው መሠረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ ሦስተኛው ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገ የመማሪያ እና የአሠራር ሥርዓቶችን መዘርጋት እንደኾነም ገልጸዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ በስፋት እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡
በክልል ደረጃ የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ ሲስተሞች እና የግንዛቤ ደረጃዎች ምን መኾን አለባቸው፣ ምንስ ይጠበቃል የሚለውን እያዘጋጀን ነው ብለዋል፡፡ አራተኛው መሠረታዊ ጉዳይ በተቋማት መካከል በቴክኖሎጂ እና በአውቶሜሽን ትስስር መፍጠር መኾኑን ነው የገለጹት፡፡ የምንገነባቸው እና የምናለማቸው እያንዳንዱ ሲስተሞች በተቋማት መካከል ያለው የተዋረድ እና የጎን ለጎን ግንኙነት የተሳሰረ ብሎም የተሳለጠ እንዲኾን የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል፡፡
አራቱ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በሰፊው ለመሥራት ብዙ ርቀት ሄደናል፤ ብዙ ፕሮጄክቶች አሉን ነው ያሉት፡፡ ፕሮጄክቶቻችን እና ሥራዎቻችን ለሚመለከታቸው አካላት እና ለማኅበረሰቡ እናደርሳለን ብለዋል፡፡ አሁን የት ላይ ነው ያለነው? የት ለመሄድ አስበናል? የሚለውንም ለማኅበረሰቡ እናስተዋውቃለን ነው ያሉት፡፡ በክልሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሲስተሞችን መሥራታቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ወደ ሥራ የገቡ እና የደኅንነት ፍተሻ እየተደረገባቸው ያሉ ሲስተሞች መኖራቸውን ነው ያመላከቱት፡፡ በክልል ደረጃ የቴክኖሎጂ መሠረተ ልማቱን ለማሻሻል እና የሚጠበቅበት ደረጃ ላይ ለማድረስ ብዙ ሥራዎችን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡ በአሠራር ሥርዓት እና በመመሪያ ዝግጅትም በርካታ ሂደቶችን መሄዳቸውን ነው የገለጹት፡፡
ብዙ ተቋማትን ያስተሳሰረ ብዙ ሲስተሞች እንዳሏቸውም ተናግረዋል፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ሠርተናል ነገር ግን መሄድ ከሚገባን አንጻር አልሄድንም ነው ያሉት፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ በክልል ደረጃ በግንዛቤውም፣ በመሠረተ ልማቱም፣ በእርስ በእርስ ትስስሩም መደረስ ከሚገባው ቦታ እንደርሳለን ብለዋል፡፡
በክልል ደረጃ የሚደረጉ የስማርት ሲቲ ግንባታዎች እና መሠል ሥራዎች ያለ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ዕውቅና ውጭ እንዳይሠሩ ወደ አንድ ማዕቀፍ መምጣታቸውን ነው ያብራሩት፡፡ የስማርት ሲቲ ግንባታ እና መሠል ሥራዎች ሲታሰቡ በተቋሙ ይሁንታ እና ድጋፍ ይፈጸማሉ ብለዋል፡፡ የሚደረጉ የቴክኖሎጂ ማስፋፋሪያ ሥራዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው እና መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረጉ እንዲኾኑ እየሠሩ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡
የስማርት ሲቲ ግንባታ አንዱ አካል እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በቁጥጥር ስር እንዲገባ ማድረግ መኾኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ መሠረተ ልማቱን የከተማውን ውበት በሚመጥን መልኩ መዘርጋት እና የተዘረጋውን ቴክኖሎጂ ለሚፈለገው ዓላማ ማዋል ተጨማሪ ሥራ ነው ብለዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎች አስፈላጊውን ዓላማ እንዲያሳኩ አስተማማኝ ዝግጅት መኖሩንም አመላክተዋል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!