
ባሕር ዳር: ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በ2017 ዓ.ም ከ133 ሺህ ኩንታል በላይ የቡና ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በ2017 በጀት ዓመት ትኩረት ከተሰጣቸው የልማት ሥራዎች ውስጥ የቡና ልማት አንዱ ነው። አርሶ አደሮችም ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውን ነግረውናል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የደቡብ አቸፈር ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር በጎሰው ዓለም እንዳሉት ወደ ቡና ልማት ከገቡ ከ20 ዓመት በላይ አስቆጥረዋል። አርሶ አደር በጎሰው ወደ ቡና ልማት ሲገቡ በ120 የቡና ችግኝ ነበር የጀመሩት። ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በባሕር ዛፍ ተሸፍኖ የነበረው ማሳቸውን በማንሳት በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ቡናን እያለሙ ይገኛሉ። ባለፉት አምስት ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ እስከ 700 ሺህ ብር ገቢ እንደሚያገኙ ነግረውናል።
ከቡና ምርት በሚያገኙት ገቢ ከተማ ላይ ቦታ ገዝተዋል። በቀጣይም ወደ ግንባታ ለመግባት አቅደዋል። ለአካባቢው አርሶ አደሮች አርዓያ መኾንም ችለዋል። ከቡና ልማቱ ባለፈ በቡናው ውስጥ ቅመማ ቅመሞችን ጭምር በማምረት ተጠቃሚ ኾነዋል። ለቡናው ጥላ እንዲኾን ሀገር በቀል ዛፎችን የመትከል ባሕል እንዲያዳብሩም አድርጓቸዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልት፣ ፍራፍሬ እና የመስኖ ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው በአማራ ክልል ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ቡናን በኩታ ገጠም እና በተፋሰስ ላይ የማልማት ሥራ እየተሠራ ይገኛ ብለዋል። ዳይሬክተሩ እንዳሉት ባለፉት አምስት ዓመታትም በ21 ወረዳዎች ላይ በኩታ ገጠም የማልማት ሥራ እየተሠራ ነው።
ማቻከል፣ ጎዛመን፣ ባሕር ዳር ዙሪያ፣ ሜጫ፣ ቡሬ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ደራ ወረዳ ቡና ከሚመረትባቸው ወረዳዎች ውስጥ ተጠቃሾች ስለመኾናቸው ነው የሚገልጹት። በየዓመቱ በአማካኝ 7 ሚሊዮን የቡና ችግኝ በማዘጋጀት 2 ሺህ 800 ሄክታር መሬት በአዲስ እየተሸፈነ ይገኛል። እስከ 2016 ዓ.ም ድረስም 31 ሺህ 463 ሄክታር መሬት በቡና ተሸፍኗል።
ከዚህ ውስጥ 22 ሺህ 256 ሄክታሩ ምርት እየሰጠ ይገኛል። በዚህ ዓመት 133 ሺህ 550 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል። ክልሉ ቡናን የሚያመርተው በመስኖ መኾኑ ከሌሎች ክልሎች የተለየ ያደርገዋል ያሉት ዳይሬክተሩ አርሶ አደሮች የተለያዩ ቅመማ ቅመሞችን ከቡና ጋር እንዲያመርቱ በመደረጉ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ተችሏል። ሥነ ምሕዳርን የመጠበቅ ዕድልም ፈጥሯል።
በክልሉ የክላስተር እና ተፋሰስ ልማት ከጀመረ ጀምሮ የባለሙያ ዕውቀት፣ የአርሶ አደሩን የማምረት እና የመንከባከብ ልምድ ማሳደግ ተችሏል ብለዋል። በክልሉ ከ2 ሺህ 200 በላይ በመንግሥት፣ በግል፣ በማኅበራት እና በተቋማት ችግኝ ጣቢዎች የቡና እና ፍራፍሬ ችግኞችን የማዘጋጀት ሥራ እየተሠራ ይገኛል። በክልሉ በቡና ልማት 488ሺህ 156 አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሲኾኑ ከዚህ ውስጥ 46ሺህ 988 ሴቶች ናቸው።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!