“የሕዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትኩረት እየተሠራ ነው ” አቶ እንድሪስ አብዱ

12

ከሚሴ: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባቲ ወረዳ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የተገነቡ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ኾነዋል። ፕሮጀክቶቹ በዓለም ባንክ እና በመደበኛ ገቢ የተገነቡ ሲኾን ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት ከኾኑት ፕሮጀክቶች መካከል የፍትሕ ተቋማት ቢሮ ግንባታ፣ የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ እና የመስኖ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል።

የባቲ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ መሐመድ አብዱ በወረዳው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ በኾነ ወጭ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ መቻላቸውን ገልጸው በበጀት ዓመቱም በርካታ ፕሮጀክቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል። የኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አሥተዳዳሪ አሕመድ አሊ ፕሮጀክቶቹ ተጀምረው እስኪጠናቀቁ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል።

የልማት ሥራዎችን መከወን የሚቻለው ሰላም ሲረጋገጥ በመኾኑ አሁን ያለውን አንፃራዊ ሰላም ወደተሟላ ሰላም ለማሸጋገር ሕዝብን ያሳተፈ ሥራ እየተሠራ መኾኑን አስረድተዋል። የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ጥሩ ደረጃ ላይ መኾናቸውን ገልጸው የክልሉ መንግሥት የሕዝብን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እየሠራ ነው ብለዋል።

ዘጋቢ:- ይማም ኢብራሂም

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበሰሜን ሸዋ ዞን የሰፈነው ሰላም በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ተጠናከሮ መቀጠሉ ተገለጸ።
Next articleየአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አጓጊ ኾኖ ቀጥሏል።