
ጎንደር፡ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በወቅታዊ የሰላምና የፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከዳባት ከተማ ማኀበረሰብ ጋር ውይይት ተካሂዷል። በውይይቱ በየደረጃው ያሉ የመንግሥት ኀላፊዎች እና የከተማው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል። ተሳታፊዎች የተለያዩ የመልካም አሥተዳደር ችግሮችን እና የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮችን አንስተው ተወያይተዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አማካሪ ግዛት ዐቢዩ ውጤታማ ውይይት መካሄዱን አንስተዋል። በሰሜን ጎንደር ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እና ከተማ አሥተዳደሮች መሰል ማኅበረሰብ አቀፍ ውይይቶች መካሄዳቸውንም ጠቁመዋል። ውይይቱ ሕዝብና መንግሥትን ከማቀራረብ አንፃር ፋይዳው የጎላ ነውም ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም እንደማኅበረሰብ ሰላም ተቀዳሚ ምርጫችን ነው ሲሉ ለአሚኮ ተናግረዋል። ተሳታፊዎቹ በውይይት መድረኩ እንዳነሱት እየተካሄደ ያለው ሰላምን የሚያውክ እንቅስቃሴ የአማራን ሕዝብ የማይመጥን እና ሊታረም የሚገባው አካሄድ ነው ብለዋል። በቀጣይም ከመንግሥት የጸጥታ መዋቅር ጎን ሆነው የአካባቢያቸውን ሰላም ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!