ሀገራዊ ሰላምን ለማጽናት በአንድነት መቆም እና በውስጣዊ መነሳሳት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

17

ደሴ: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ከመንግሥት ሰራተኞች ጋር በደሴ ከተማ ውይይት ተካሂዷል። የክልሉን የሰላም እጦት ችግሮች ለመቀልበስ የተሠሩ የፀጥታ፣ የሕዝብ ግንኙነት፣ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት ያመጡትን ዉጤቶች በማፅናት በክልሉ ዉስጥ ዘላቂ ሰላም መገንባት የሚያስችል መተማመን ለመፍጠር ያለመ መድረክ ነው የተካሄደው። በመድረኩ በደሴ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ ዓለማየሁ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ801ኛ ኮር ዋና አዛዥ ጀነራል ዘውዱ ሰጥአርጌ እና የተለያዩ የመንግሥት ሠራተኞች ተሳትፈዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በሚነሱ ግጭቶች የመንግሥት ሠራተኞች ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየገቡ ነው ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች በገጠሙን ዉስጣዊ ችግሮች ላይ በግልጽ ተነጋግሮ የአመለካከት አንድነት መፍጠር ይገባል ብለዋል። አሁን በክልሉ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለመፍታት መሰል የውይይት መድረኮች መካሄዳቸው ፋይዳቸው የላቀ መሆኑንም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል።

በደሴ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ ዓለማየሁ የሀገር እድገትና ኅልውናን ለማስቀጠል ሰላም አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል። አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሚያጋጥሙንን የጽንፈኝነት እሳቤዎች በውል ተረድቶ በድል የመሻገር አቅጣጫ ላይ ግንዛቤ መያዝ እንደሚያስፈልግ አቶ አሸናፊ ጠቁመዋል፡፡ ሰላም ጠል በኾኑ አካላት ላይ የሚወሰደውን ሕጋዊ እርምጃ በመደገፍ ሀገራዊ ሰላሙን ለማጽናትና ለዘላቂነቱም በጋራ ለመረባረብ የሁሉም ውስጣዊ መነሳሳት ያስፈልጋል ሲሉም አንስተዋል።

ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሀገራዊ ሰላምን ለማጽናት በአንድነት መቆም እና በውስጣዊ መነሳሳት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።
Next articleበክልሉ የተከሰተው ሰላምን የሚያውክ እንቅስቃሴ የአማራን ሕዝብ የማይመጥን እና ሊታረም የሚገባው አካሄድ መኾኑን የዳባት ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።