ሀገራዊ ሰላምን ለማጽናት በአንድነት መቆም እና በውስጣዊ መነሳሳት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

27

ደሴ: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ከመንግሥት ሠራተኞች ጋር በደሴ ከተማ ውይይት ተካሂዷል። የክልሉን የሰላም እጦት ችግሮች ለመቀልበስ የተሠሩ የፀጥታ፣ የሕዝብ ግንኙነት፣ የልማትና የመልካም አሥተዳደር ተግባራት ያመጡትን ዉጤቶች በማፅናት በክልሉ ዉስጥ ዘላቂ ሰላም መገንባት የሚያስችል መተማመን ለመፍጠር ያለመ መድረክ ነው የተካሄደው።

በመድረኩ በደሴ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ አለማየሁ፣ በሀገር መከላከያ ሠራዊት የ801ኛ ኮር ዋና አዛዥ ጀኔራል ዘውዱ ሰጥ አርጌ እና የተለያዩ የመንግሥት ሠራተኞች ተሳትፈዋል። በተለያዩ ጊዜያት በሚነሱ ግጭቶች የመንግሥት ሠራተኞች ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየገቡ ነው ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች በገጠሙን ዉስጣዊ ችግሮች ላይ በግልጽ ተነጋግሮ የአመለካከት አንድነት መፍጠር ይገባል ብለዋል።

አኹን በክልሉ የተፈጠረውን አለመረጋጋት ለመፍታት መሰል የውይይት መድረኮች መካሄዳቸው ፋይዳቸው የላቀ መኾኑንም ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል። በደሴ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አሸናፊ አለማየሁ የሀገር እድገትና ህልውናን ለማስቀጠል ሰላም አስፈላጊ መኾኑን ገልጸዋል። አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሚያጋጥሙንን የጽንፈኝነት እሳቤዎች በውል ተረድቶ በድል የመሻገር አቅጣጫ ላይ ግንዛቤ መያዝ እንደሚያስፈልግ አቶ አሸናፊ ጠቁመዋል፡፡ ሰላም ጠል በኾኑ አካላት ላይ የሚወሰደውን ሕጋዊ እርምጃ በመደገፍ ሀገራዊ ሰላሙን ለማጽናትና ለዘላቂነቱም በጋራ ለመረባረብ የሁሉም ውስጣዊ መነሳሳት ያስፈልጋል ሲሉም አንስተዋል።

ዘጋቢ:- ሰልሀዲን ሰይድ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ያጣነውን ሠላም ለመመለስ ከመቸውም ጊዜ በላይ በጋራ መነጋገርና መወያየት ይጠበቅብናል” አቶ ደጀን አከለ
Next articleሀገራዊ ሰላምን ለማጽናት በአንድነት መቆም እና በውስጣዊ መነሳሳት መሥራት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።