
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር እና የላይ ጋይንት ወረዳ አሥተዳደር “ሠላም ለሁሉም ሁሉም ለሠላም” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገራዊ፣ ሕዝባዊና ወቅታዊ የሠላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው፡፡
የነፋስ መውጫ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ደጀን አከለ በከተማ አሥተዳደሩ ሠላምን ለማስፈን፣ ልማትን ለማሳለጥ እና የሕዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
ጽንፈኛው ኃይል በሕዝባችን ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳትና አሉታዊ ተፅዕኖው በቃላት አይገለፅም ነው ያሉት። በዚህም የሕዝብን ስቃይ፣ ሞት፣ እገታና መፈናቀል እንደ መዝናኛ የሚቆጥር አረመኔነቱን አስመስክሯል ብለዋል፡፡
ጦርነት ለማንም የማይጠቅምና ሀገርን ወደ ኋላ የሚያስቀር እኩይ ተግባር በመኾኑ ያጣነውን ሠላም ለመመለስ ከመቸውም ጊዜ በላይ በጋራ መነጋገር እና መወያየት ይጠበቅብናል ማለታቸውን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!