
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በወልቃይት ወረዳ ወፍ አርግፍ ከተማ “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው። በመድረኩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች እየተሳተፉ ነው።
በኮንፈረንሱ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ አማረ ሰጤ፣ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አዲሱ ማለፊያው፣ ብርጋዴል ጀኔራል ምልኬሳ አብዲሳ፣ የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተገኝተዋል።
ጦርነት የሰዎችን ሕይወት የሚያጠፋና ንብረትን የሚያወድም ብሎም የማኅበረሰብን ነጻነት የሚቀማ ነው ያሉት ምክትል አፈ ጉባኤው ችግሮችን በንግግር በመፍታት በልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባም ተናግረዋል።
ከተለያዩ የወረዳው ቀበሌዎች የተወጣጡ የማኅበረሰብ አካላትም የመጨረሻው ምሽጋችን ከኾነው ከመከላከያ ሠራዊታችን ጎን ተሰልፈን ለሰላማችን ዘብ እንቆማለን ብለዋል። በግጭት የሚጠብቅ እንጂ የሚፈታ ችግር ባለመኖሩ ጥያቄዎች በውይይት ብቻ እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረባቸውን ከወልቃይት ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!