
ደሴ: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ወሎ ዞን በጃማ እና ወረኢሉ ወረዳዎች በኩታገጠም የለማ የስንዴ ሰብልን በርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሚመራ የክልል እና የዞን የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ልዑክ ጎብኝቷል። በደቡብ ወሎ ዞን የጃማ ወረዳ አርሶ አደሮች የተሻሻለ ምርጥ ዘር እና የባለሙያ ምክርን በመጠቀም በመሥራታቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ነው የተናገሩት።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ በዞኑ በ2016/2017 የመኸር ምርት ዘመን ከ14 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ወደ 8 ሚሊዮን ኩንታል የሚኾነው ከስንዴ ሰብል የሚገኝ ነው ብለዋል። ዛሬ የተጎበኘው በጃማ ወረዳ 18 ቀበሌ 628 ሄክታር ሽፋን ያለው የስንዴ ኩታገጠም በጥሩ ቁመና ላይ ይገኛል ነው ያሉት።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አሥተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ በ2016/2017 የመኸር ምርት ዘመን 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር የሚጠጋ መሬት በዘር ተሸፍኗል ብለዋል።
በዚህም አስፈላጊው ግብዓት በመቅረቡ እና የባለሙያ ድጋፉም ከፍተኛ ስለነበር ከዕቅድ በላይ ምርት እንደሚገኝ የሰብል ቁመና ትንበያው ያሳያል ነው ያሉት።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የሕዝቡን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ መሪዎች እና ባለሙያው ከአርሶ አደሩ ጋር ተቀናጅተው በመሥራታቸው በክልሉ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ይጠበቃል ነው ያሉት።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በወረኢሉ እና ጃማ ወረዳዎች የተመለከቱት የሰብል ቁመና በክልሉ የተሻለ ምርት እንደሚገኝ ማሳያ የሚኾን እንደኾነ ነው ያብራሩት።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!