“የተዋረድ ምክር ቤቶች ሕግ እና አሠራሮች እንዲከበሩና ሰላም እንዲሰፍን አሥፈጻሚውን አካል ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ይገባቸዋል” ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)

52

ደብረታቦር: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ምክር ቤት የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ትውውቅ እና የ1ኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ ክንውን በደቡብ ጎንደር ዞን ከሚገኙ የከተማ እና የወረዳ ምክር ቤቶች ጋር በደብረ ታቦር ከተማ አካሂዷል። በመድረኩ በየደረጃው ያሉ የከተማ እና የወረዳ ምክር ቤት አፈ ጉባኤዎች እና ቋሚ ኮሚቴዎች ተሳትፈዋል። የ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ እና የ1ኛ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

የደብረታቦር ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ኃይለኢየሱስ ሰለሞን በ2017 በጀት ዓመት በየተቋማቱ የታቀዱ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ዕቅዶች በተገቢው ሁኔታ ስለመከናወናቸው ምክር ቤቶች ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ አለባቸው ብለዋል። ምክትል ከንቲባው የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል በሚደረገው ሥራ ኅብረተሰቡን በማወያየት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባልም ነው ያሉት።

ሕዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ጥያቄዎችን ለመፍታት እና ሰላምን ለማረጋገጥ ምክር ቤቶች በትኩረት መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል። በአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ ፍትሕ እና አሥተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሠብሣቢ ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር) የተዋረድ ምክር ቤቶች ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሕግ እና መመሪያዎችን በማውጣት የሕዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይገባቸዋል ብለዋል።

በአሥፈጻሚው አካል ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ሰላም እንዲሰፍን እና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥም የምክር ቤቶች ሚና ከፍ ያለ እንደኾነም አስገንዝበዋል። በ2017 በጀት ዓመት ጠንካራ የምክር ቤት አባላትን በመፍጠር ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እና በሁኔታዎች የማይናወጥ ተቋም እንዲገነባ አበክሮ መሥራት ያሰፈልጋልም ብለዋል።

በክልሉ ብሎም በየአካባቢያቸው ሰላም እንዲሰፍን ሚናቸውን እንደሚወጡ እና አሥፈጻሚ አካሉን በመከታተል እና ቁጥጥር በማድረግ የእንደራሴነት ሚናቸውን እንደሚወጡም የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ በየአካባቢው ያለው የጸጥታ ችግር ሥራዎችን በተገቢው መልኩ ለመሥራት እና ክትትል እና ቁጥጥር ለማድረግ አዳጋች እንደኾነም በውይይቱ ተነስቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ጋር በጋራ ሥንሠራ ለኅብረተሰቡ ፈጣን መረጃ ለመስጠት ያስችለናል” የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ
Next articleሰላምን ሊያስከብር የሚችለው የሰላሙ ባለቤት ማኅበረሰቡ እንደኾነ የኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳደር ገለጸ።