“ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ጋር በጋራ ሥንሠራ ለኅብረተሰቡ ፈጣን መረጃ ለመስጠት ያስችለናል” የአሚኮ ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ

48

ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን እና የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አብረው ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱን የተፈራረሙት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ እና የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቤል ፈለቀ ናቸው፡፡

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ራሱን ከዘመኑ ቴክኖሎጂዎች ጋር እያወዳጀ ቀዳሚ፣ ዕውነተኛ እና ሚዛናዊ የኾኑ የዘገባ ሥራዎችን ይሠራል፡፡ ዛሬን ከትናንት እያሻሻለ፤ ነገን ደግሞ ከዛሬ ለማሻሻል ሩቅ ጉዞ አስቦ በታላቅ ራዕይ የሚሠራ ተቋም ነው፡፡ ተቋሙ ሃሳቦቹን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ተደራሽ ለማድረግ እና ለሀገር ታላቅ አስተዋጽኦ ለማድረግ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋማት ጋር በቅርበት ይሠራል፡፡

የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ ሙሉቀን ሰጥዬ የቴክኖሎጂ ዕድገት እና አቅርቦት ለሚዲያ ሥራ ፋይዳው ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ጋር በጋራ ሥንሠራ ለኅብረተሰቡ ፈጣን መረጃ ለመስጠት ያስችለናል ነው ያሉት፡፡ መረጃዎቹን በጥራት እና በፍጥነት ለማሰራጨት በአንድ ጊዜ ብዙ ቦታዎች ላይ ለመድረስ ቴክኖሎጂ ወሳኝ መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ሰው ላይ የደረሱት መረጃዎች የሰው ሕይወትን በመቀየር በኩል ያላቸውን ተጽዕኖ ለማየት ቴክኖሎጂን በየጊዜው እያሻሻልን መጠቀም ያስፈልገናል ብለዋል፡፡ ከሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ጋር አብሮ መሥራት የማይተካ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል፡፡ የሚዲያ አማራጮችን ሁሉ ተጠቅመን ለሕዝብ መድረስ የምንችለው ቴክኖሎጂን መጠቀም ስንችል ነው ብለዋል፡፡

አሚኮ በሁለቱ የቴሌቪዥን ቻናሎች፣ በሬዲዮ ማሰራጫ ጣቢያዎች፣ በዲጂታል ሚዲያ እና በሌሎች ሚዲየሞች መረጃዎችን ለመሠብሠብ፣ ለማቀናበር እና ለማስተላለፍ ቴክኖሎጂዎችን እንደሚጠቀም ነው ያነሱት፡፡ አሚኮ በሚያስተላልፍባቸው 11 ቋንቋዎች የዲጂታል ሚዲያ አገልግሎት እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡ አሚኮ ውጤታማ ሥራ እንዲሠራ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን እንደራሱ ተቋም በመቁጠር የሚዲያ ቴክኖሎጂ ድጋፍ እንዲያደርግም ጠይቀዋል፡፡

አሚኮ የክልሉ ሕዝብ የመረጃ ቋት መኾኑንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡ ተቋሙ ቀደም ሲል የነበሩ መረጃዎችን ወደ ዲጂታላይዝ ለመቀየር የሚያደርገውን ሥራ በማገዝ ረገድ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን በባለቤትነት እንደሚሠራ ያላቸውን ዕምነት ገልጸዋል፡፡

ዘመኑ ለሐሰተኛ መረጃዎች የተጋለጠ መኾኑን ያመላከቱት ዋና ሥራ አሥፈጻሚው ሐሰተኛ መረጃዎችን ለመከላከል እና የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ የኅብረተሰቡን የሚዲያ ግንዛቤ ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡ ቴክኖሎጂዎች ማኅበረሰቡን የሚጠቅሙ እንጂ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ እንዳይኾኑ ኮሚሽኑ በአሚኮ አማካኝነት የማስተማር እና የማስገንዘብ ሥራ መሥራት እንደሚገባውም ተናግረዋል፡፡ አሚኮ የሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን የሥራ እንቅስቃሴዎች ለሕዝቡ በማድረስ በኩልም በጋራ እንደሚሠራ ነው ያመላከቱት፡፡

የአማራ ክልል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቤል ፈለቀ ለአሚኮ ከሰው ኀይል የአቅም ግንባታ ጀምሮ በመሠረተ ልማቶች እና ሌሎች ሥራዎች ላይ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉም ነው ያብራሩት፡፡ ድጋፍ የሚደረገው እንደ ትብብር ሳይኾን በባለቤትነት ስሜት አሚኮ መድረስ የሚገባው ደረጃ ላይ እንዲደርስ ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡

የሰው ኀይሉን በማጠናከር፣ ለሚዲያ የሚያስፈልጉ ሶፍትዌሮችን እና ሲስተሞችን በማስታጠቅ አስፈላጊ ሥልጠናዎችን ለመስጠት ዝግጅ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ ከአሚኮ ጋር በትብብር እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ አሚኮ ማድረግ የሚገባውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የተመራ የክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተካተቱበት ልዑክ በደቡብ ወሎ ዞን ጃማ ወረዳ የሰብል ጉብኝት አካሄደ።
Next article“የተዋረድ ምክር ቤቶች ሕግ እና አሠራሮች እንዲከበሩና ሰላም እንዲሰፍን አሥፈጻሚውን አካል ክትትል እና ቁጥጥር ማድረግ ይገባቸዋል” ደሴ ጥላሁን (ዶ.ር)