
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ለሁሉም የፍራፍሬ አይነቶች ተስማሚ የኾነ የአየር ንብረት የያዘ ክልል እንደኾነ ይነገራል። በክልሉ የፍራፍሬ ልማት ቀደም ብሎ ቢጀመርም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተደራጀ መንገድ እየለማ መኾኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ ያሳያል። ከሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የአርሶ አደሮችን ሥርዓተ ምግብ ለማሻሻል በጓሮ ልማት እንዲያተኩሩ ተደርጓል።
በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጓንጓ ወረዳ በአቮካዶ ልማት ላይ የሚገኙት አርሶ አደር ዘመኑ ሳልለው አንዱ ናቸው። አርሶ አደሩ ላለፉት ስድስት ዓመታት ያህል በአንድ ሄክታር የወል ተፋሰስ መሬት ላይ በማኅበር እያለሙ ይገኛሉ። በዚህ ዓመት ተጨማሪ አንድ ሄክታር ለማልማት በዝግጅት ላይ ናቸው።
በማኅበር ከሚያለሙት ባገኙት ውጤት በሩብ ሄክታር የግል መሬታቸው ላይ አቮካዶ እና ሙዝ እያለሙ መኾናቸውንም አቶ ዘመኑ ነግረውናል። በዚህ ዓመት የተሻለ ምርት እንደሚያገኙም ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና መስኖ ልማት ዳይሬክተር ይበልጣል ወንድምነው እንዳሉት በአማራ ክልል የፍራፍሬ ልማት ቀደም ብሎ ቢጀመርም ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በኩታ ገጠም፣ ተፋሰስ እና የጓሮ ልማትን መሠረት ያደረገ ሥራ እየተሠራ ይገኛል። ባለፉት ስድስት ዓመታት በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ለፍራፍሬ ልማት በመመደብ የቆላ ፍራፍሬ ብቻ ከ5 ሚሊዮን ሚልዮን በላይ ችግኝ በማዘጋጀት የማልማት ሥራ እየተሠራ ነው።
በአጠቃላይ በክልሉ እስከ 2016 ዓ.ም 66 ሺህ 574 ሄክታር መሬት በፍራፍሬ ተሸፍኗል። ከ1 ሚሊዮን 496 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተሳታፊ ናቸው። በፍራፍሬ ከተሸፈነው ማሳ ውስጥ ደግሞ 39 ሺህ 808 ሄክታሩ ምርት በመስጠት ላይ ይገኛል። በዚህ ዓመትም 5 ሚሊዮን 938 ሺህ 128 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በአማራ ክልል ባለፉት ስድስት ዓመታት ከኩታ ገጠም ልማት ባለፈ ችግሮችን መቋቋም የሚችሉ የፍራፍሬ ዝርያዎችን በተፋሰሶች ላይ የማልማት ሥራ እየተሠራ ነው። ከሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ አርሶ አደሮች ሥርዓተ ምግባቸውን እንዲያሻሽሉ ለጓሮ ልማት ትልቁን ድርሻ ተሰጥቶ እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመት በ289 የመንግሥት፣ በ1919 የግል፣ በ37 የማኅበራት እና በ13 የተቋማት ችግኝ ጣቢዎች ላይ 13 ሚሊዮን የቡና እና ፍራፍሬ ችግኝ በማዘጋጀት በ14 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ማልማት ተችሏል ብለዋል። ከዚህ ውስጥ 50 በመቶ የሚኾነው ሽፋን የጓሮ ልማት ነው። በዚህ ዓመትም 20 ሚሊዮን ችግኝ በ20 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል ቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ይገኛል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!