የቆቦ ጊራና የመስኖ ፕሮጄክት ወደ ማልማት ተመልሷል፡፡

37

ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት ከቆቦ ጀምሮ አስከ ጊራና የከርሰ ምድር ውኃን መሠረት በማድረግ እያለማ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ተቋም ነው፡፡ የቆቦ ጊራና የመስኖ ፕሮጄክት በሰሜኑ ጦርነት ጉዳት ከደረሰባቸው የልማት ተቋማት መካከልም አንዱ ነው፡፡

ከጦርነቱ በፊት በ2 ሺህ 807 ሄክታር ማሳ በዓመት ሦስት ጊዜ ያመርት እንደነበር የቆቦ ጊራና ሸለቆ ልማት ፕሮግራም ጽሕፈት ቤት የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አንዳርጌ አስማረ ገልጸዋል፡፡ በጦርነቱ ምክንያት ከ65 የመስኖ ፕሮጀክቶች ውስጥ 40 የመስኖ ፕሮጀክቶች ከአገልግሎት ውጭ እንደኾኑ ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

በወደሙት የፕሮጀክቱ ቁሳቁሶች ምክንያት 1ሺህ 218 ሄክታር መሬት እስከ አሁን ማልማት አልተቻለም፡፡ በዚህ ሄክታር መሬት ውስጥ በዓመት ሦስት ጊዜ ሊያመርቱ የሚችሉ አርሶ አደሮች ከሥራ እና ከምርት ውጭ ኾነዋል፡፡

እነዚህ አርሶ አደሮች በአንድ ጊዜ ምርት ብቻ 55 ሺህ 583 ኩንታል ምርት ማምረት ይችሉ ነበር፡፡ አሁን ላይ በጦርነት ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች ውስጥ 25 የሚኾኑ የመስኖ አውታር እና የኤሌክትሮ መካኒካል ጥገናዎችን በማድረግ ወደ ሥራ በመግባት የመስኖ ልማት ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በዚህም በአጭር ጊዜ የሚደርሱ ገበያ ተኮር ሰብሎችን፣ አትክልት እና ቋሚ ፍራፍሬዎችን እያለማም ይገኛል፡፡

አርሶ አደሮች በዘመናዊ መስኖ ልማት ከአካባቢው ሥነ-ምሕዳር ጋር የሚጣጣሙ ገበያ ተኮር ሰብሎችን እንዲያላምዱ እና በዓመት ሦስት ጊዜ እንዲያመርቱ በማስቻል ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምሩ አስተዋጽኦ እያደረገ ስለመኾኑም ነው የተገለጸው፡፡

አማራጭ የገቢ ምንጮችን በማስፋት የአርሶ አደሮችን የኑሮ ደረጃ የማሻሻል ሥራም እየሠራ ስለመኾኑ ተጠቁሟል፡፡ ፕሮጀክቱ በኢኮኖሚ የበለፀገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ትኩረት አድርጎ በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡

በእነዚህ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአንደኛ እና በሁለተኛ ዙር 1ሺህ 588 ሄክታር መሬት ማልማት ተችሏልም ብለዋል፡፡

ይህ የምርት ውጤት አካባቢው ካለው የመልማት አቅም አንጻር ሲታይ ጥቂት መኾኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ከፌዴራል መንግሥት እና ከግብርና ቢሮ ጋር በመነጋገርም 26 ትራንስፈርመሮችን ለማስገባት በዝግጅት ላይ እንደኾኑም ገልጸዋል፡፡

ዳይሬክተሩ የሚመለከተው አካል አሁን ካለው በላይ ድጋፍ እና ክትትል ቢያደርግ እና ለመስኖ ልማት የሚውሉ መሬቶች ሙሉ በሙሉ በሰብል ቢሸፈኑ ለክልሉ ብሎም ለሀገር የምግብ ፍጆታ ግብዓት አይነተኛ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ነው ያብራሩት፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ዓለምን ከረሃብ ነጻ ለማድረግ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት 50 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል” ዳይሬክተር ጄኔራል ገርድ ሙለር
Next article“በ2017 በጀት ዓመት ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የፍራፍሬ ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል” የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ