“ዓለምን ከረሃብ ነጻ ለማድረግ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት 50 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ያስፈልጋል” ዳይሬክተር ጄኔራል ገርድ ሙለር

57

አዲስ አበባ: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ከርሃብ ነጻ የኾነ ዓለም መፍጠር” በሚል መሪ መልዕክት ዓለምአቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እየተካሄደ ነው። በኮንፈረንሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት እና የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ዳይሬክተር ጄኔራል ገርድ ሙለር፣ የአቡዳቢ አልጋወራሽ ግርማዊ ሼህ ኻሊድ ቢን መሐመድ ቢን ዛይድ እንዲሁም ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ከ30 በላይ ከትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት የተውጣጡ ከ1 ሺህ 500 በላይ ተሳታፊዎች በኮንፈረንሱ ታድመዋል፡፡

የተመድ የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት (ዩኒዶ) ዳይሬክተር ጄኔራል ገርድ ሙለር አፍሪካ በተፈጥሮ ሃብቶች የበለጸገች እንደመኾኗ ያላትን እምቅ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸዋል። የዓለም የምግብ ዋስትናን ችግር ለመፍታት በግብርናው ዘርፍ ምርት እና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችን መጠቀም እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ዓለምን ብሎም አፍሪካን እየፈተነ መኾኑን የገለጹት ዳይሬክተር ጄኔራሉ ኮንፈረንሱ ችግሩን ከመሠረቱ ሊፈቱ የሚችሉ የመፍትሔ ሃሳቦችን በጋራ ለማስቀመጥ እና ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችል ነው ብለዋል። ዓለምን ከረሃብ ነጻ ለማድረግ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት 50 ቢሊዮን ዶላር ተጨማሪ ኢንቨስትመንት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።

የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ከረሃብ ነጻ የኾነች ዓለም ለመፍጠርም ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት አለባቸው ብለዋል። ለሦስት ቀናት የሚካሄደውን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ዩኒዶ፣ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ አዘጋጅተውታል።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleአንድነት ታጸናለች፣ አንድነት ታስከብራለች
Next articleየቆቦ ጊራና የመስኖ ፕሮጄክት ወደ ማልማት ተመልሷል፡፡