
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) አንድነትን የጠበቁ በኩራት ኖረዋል፤ በጠላቶቻቸው ፊት ተከብረዋል፤ ነጻነታቸውን አስከብረዋል፤ ሉዓላዊነታቸውን አጽንተዋል፤ የከበረ ታሪክ ሠርተዋል፤ አንድነታቸውን ለተነጠቁ ምሳሌና አርዓያ ኾነዋል፡፡
አንድነት ከዓለት የጠነከረ አድርጋ ታጸናለች፤ አንድነት ታስከብራለች፤ አንድነት እሴትን ትጠብቃለች፣ ባሕልን ታሳድጋለች፡፡ አንድ የኾኑት አጀብ የሚያሰኝ ገድል ፈጽመዋል፤ አንድ የኾኑት ከተራራ የገዘፈ ታሪክ አኑረዋል፤ የልጅ ልጅ የሚኮራበት የኩራት ታሪክ ጽፈዋል፤ ወዳጅ የሚመካበት ሐውልት አቁመዋል፡፡
አንድነት ያላቸው ወሰናቸው የጠበቀ፣ ክብራቸው የተጠበቀ ነው፡፡ አንድነት የሌላቸው በጠላቶቻቸው ይጠቃሉ፤ ባሕሎቻቸውን በጠላቶቻቸው ይወረሳሉ፤ ታሪካቸውን ይነጠቃሉ፤ እሴቶቻቸውን ይቀማሉ፤ ሀገራቸውን ለጠላቶቻቸው አሳልፈው ይሰጣሉ፡፡
አንድነት የሌላቸው ራሳቸውን ለቅኝ ግዛት አሳልፈው ሰጥተዋል፤ አንድነት የሌላቸው በወላጆቻቸው ሀገር ባይተዋር ኾነዋል፤ በእርስትና በጉልታቸው ባዕዳን ሰልጥነውባቸዋል፤ በቤታቸው እና በንብረታቸው እንዳያዝዙ ተደርገዋል። ልጆቻቸው ለገበያ ሲቀርቡ በፍርሃት ውስጥ ኾነው ተመልክተዋል፤ ዳግም ላያዩዋቸው በአሻገር ተሰናብተዋል፡፡
አንድነት ያላቸው ግን የቅኝ ግዛትን ዘመን አፈራርሰዋል፤ ሊውጣቸው የመጣውን ጠላት ድባቅ መትተው መልሰዋል፤ ለወሬ ነጋሪ ሳያስቀሩ በየሸንተረሩ አስቀርተዋል፤ አንድነት ያላቸው ነጻነታቸውን ሳያስደፍሩ ኖረዋል፤ የሀገር ሉዓላዊነታቸውን ከዓለት አጠንክረው፣ ሠንደቅ ዓላማቸውን ከፍ አድርገው ዘመናትን ተሻግረዋል፤ ባሕልና እሴቶቻቸውን፣ ታሪክና ሃይማኖቶቻቸውን ጠብቀውና አስጠብቀው ኖረዋል፡፡
ኢትዮጵያን ያስከበራት የአንድት፣ ኢትዮጵያን በዓለሙ ሁሉ የተለየች ያደረጋት የኅብረት፣ የአትንኩኝ ባይነት፣ የጀግንነት፣ የጽናት፣ የነጻነት ታሪኳ ነው፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ከአንድነት ነጥሎ ማዬት አይቻልም፤ አንድነት ሲነሳ ኢትዮጵያውያን ይነሳሉ፡፡ ኅብረት ሲወሳ ኢትዮጵያውያን ይወሳሉና፡፡
ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን አብዝተው የሚወድዱ፣ ለሀገራቸውም አያሌ መስዋዕትነት የከፈሉ ጀግኖችና ኩሮዎች እንደኾኑ በታሪክ ተመስክሮላቸዋል፡፡ ዓድዋን የመሰለ የጀግንነት ድል፣ የታሪክ ሐውልት ያቆሙ በአንድነታቸው፣ በጽናታቸው፣ በጀግንነታቸው እና በአልደፈርም ባይነታቸው ነው፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ትግላችን በተሰኘው መጽሐፋቸው በዓለም ከጥቂት አይበገሬ፣ ታሪከኛና ጥንታዊ ሀገራት መካከል የእኛ ሀገር ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡ ኢትዮጵያ በጀግኖቿ የአርበኝነት ተጋድሎ በነጻነት መኖር ብቻ ሳይሆን በዓለም የታፈረችና የተከበረች ናት፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ በሀገራቸውን የሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጀግኖች አይበገሬ የአርበኝነት ተጋድሎ ገድል የሚያስረዳን አንድነት ኃይል መኾኑን፣ አንድነት ታላቅነት መኾኑን ነው፡፡ የዚህች የጥንታዊት አይበገሬ ነጻና አኩሪ ሀገር ባለቤት ለመኾን የቻልነው በአንድነታችንና በኅብረታችን ነው ብለው ጽፈዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ነጭ ሁሉ የደነገጠበትን ኃያል ታሪክ የጻፉት በአንድታቸው ነው፡፡ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ “የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ የዓድዋ ድል” በተሰኘው መጽሐፋቸው የኢትዮጵያን አንድነት እና ጀግንነት የሚያስደንቅ መኾኑን ጽፈዋል፡፡
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ኢትዮጵያውን በአንድነት ስላመጡት የዓድዋ ድል ሲጽፉ “የኢትዮጵያ ሕዝብ እንኳን ወታደሩ ባላገሩና ነጋዴውም ካህናቱ ሳይቀሩ ስለ ሀገራቸው ነጻነት ስለ ንጉሣቸው ክብር ሲሉ ሞታቸውን የማይፈሩ ጀግኖችና ቆራጦች ናቸውና የመድፉንና የጠመንጃቸውን ተኩስ ሳይፈሩ በሠልፉ ውስጥ ገቡበት፡፡
የፊተኛው ሲወድቅ የኋላኛው ወደፊት ከመገስገስ በቀር የወደቀውን ላንሳ ደክሞኛልና ልረፍ አይልም ነበር፡፡ የጦርነቱም አኳኋን አለቃውም ጭፍራውም ፍዬል እንዳየ ነብር በየፊቱ ከመሮጥና ከመግደል በቀር ባንድነት ቆሞ ለመዋጋት አያስብም ነበር፡፡ እንኳን ጭፍራ አለቆች ደጅአዝማቾችና ራሶቹም ቢኾኑ በፈረስ እየኾኑ አንደኛውን እየጋለቡ ይገድሉ ነበር፡፡ በጠመንጃ መግደልንም ከጉብዝና ስላልቆጠሩት በጎራዴ ለመግደል ይሽቀዳደሙ ነበር፡፡
ይልቁንም ተራ ወታደር ከመግደል ይልቅ የጦር አለቆችን መግደል ጀግንነት ነው እያሉ ተራውን ወታደር እያለፉ በቆቡና በልብሱ የወርቅ ምልክት ያለበትን የጦር አለቃ ይፈልጉ ነበር ” ብለው ጽፈዋል፡፡
በአንድ ጀምበር የተሠራ ነገር ግን ለዘላለም የሚያበራው የኢትዮጵያውያን ድል ዓድዋ የኢትዮጵያውያን የአንድነት ድል ነው፡፡ ከዓድዋ በፊት ከዓድዋም በኋላ የተሠሩ አያሌ የኢትዮጵያውያን የኩራት ታሪኮች የአንድነት ውጤቶች ናቸው፡፡
በዓድዋ የተሸነፈችው ኢጣሊያ ከአርባ ዓመታት በኋላ ዳግም ስትመጣ መሶሎኒ ኢትዮጵያን ቢያሸንፏት ምን ሊኾኑ ነው? ተብለው የተጠየቁት ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ “መሣሪያ ማንሳት አቅሙ የሚፈቅድለት የኢትዮጵያ ወንድና ሴት ጎልማሶች በሀገሪቱ ውስጥ እስካሉ ድረስ ሞሶሎኒ ኢትዮጵያን ድል አያደርጋትም” ነበር መልሳቸው፡፡ የኢትዮጵያዊ ሥነ ልቡናው እንዲህ ነው፡፡ እንዳሉትም ኢትዮጵያ ድል አድርጋ ነጻነቷን አስጠበቀች፡፡
ተድላ ዘዮሐንስ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ መጽሐፋቸው ኢትዮጵያ በመንግሥትነት ታሪክ ዘመን ሁሉ እንደኖረች አላከራከረም፡፡ ወገንም ጠላትም የተቀበለው ሐቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቅኝ ግዛትን ተናንቃ በማሸነፍ በነጻነት ኖራለች፡፡ ይህም ጥሩ ታሪክ የሌላቸውን ሀገራት ያስቀናቸዋል ብለው ጽፈዋል፡፡
ተድላ ዘዮሐንስ እንደሚሉት የዘር ልዩነት በሽታ የተጠናወታቸው ሀገሮች የኢትዮጵያን አንድነትና ነጻነት አይወዱም፡፡ በእርግጥ የዘር ልዩነት የተጠናወታቸው ፖለቲከኞችም የኢትዮጵያን የአንድነት ታሪክ አይወዱትም፤ አይፈልጉትም፡፡
ታዲያ ይህች ታላቅ ሀገር ከዓመታት ወዲህ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት እየተሰበከባት መከራዋ በዝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በርከት ያሉ ቋንቋዎች፣ ባሕሎች፣ ሃይማኖቶች አሉ፡፡ እነዚህን ደግሞ ለአንድነት መተሳሰሪያነት ከመስበክ ይልቅ ልዩነትን ለማስፊያ የሚጠቀሙባቸው በርክተዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአንድነት ጸንታ የኖረችን ሀገር በእጅጉ እጎዳት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ትስስርና መስተጋብር በኢትዮጵያ ታሪክ በሚል ርእስ ባሳተመው ጽሑፍ ላይ ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ “ኢትዮጵያ ረጅምና ደማቅ ታሪክ ያላት ሀገር ናት። በዚህም ስንኮራ ቆይተናል። ባንፃሩ ግን በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታሪክ የፖለቲካ ግብግብ አውድማ እየኾነ መምጣቱ ለሁላችንም ገሃድ ነው። ሀገራችንም በዘውጋዊና ክልላዊ ግጭቶች ስትናጥ ቆይታለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እየባሰ መጥቶ የሀገሪቱ ኅልውና አጠያያቂ የሆነበት ደረጃ ደርሷል። ጊዜ በወለደው አርቲፊሻል የነባርና መጤ ተቃርኖ ለአያሌ ዓመታት አብረው የቆዩ ኢትዮጵያውያን በጠላትነት መፈረጅ ጀምረዋል። ሰዎች ለረጅም ዘመናት ከኖሩበትና አንዳንዴም ከተወለዱበት ቀዬ ከመፈናቀልም አልፈው በግፍ ተጨፍጭፈዋል።
ታሪካዊ ሐቁ ግን ከዚህ በእጅጉ የተለየ ነው። የታሪክ ሰነዶችና ማስረጃዎቸ የሚያመለክቱን የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችና ክልሎች፣ ምንም እንኳን የማንነታቸው መገለጫ የሆኑ ባሕርያትና ተቋማት ቢኖሯቸውም፣ በብዙ መንገድ እርስ በርስ የተሳሰሩና የተጋመዱ እንደነበሩ ነው” ብለዋል፡፡ የልዩነት ዘር ደግሞ ሀገርን በእጅጉ እየጎዳ መኾኑ ነው ምሁሩ ያመላከቱት፡፡
ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የኢትዮጵያ የታሪክ ባለሙያዎች ማኅበር ከተቋቋመበት ዓላማዎች አንዱ ታሪክና የታሪክ ትምህርት ለብሔራዊ መግባባት ስለሚውልበት ኹኔታ ሙያዊ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው ብለዋል፡፡
በታሪካችን ብዙ ግፎች መፈፀማቸውን የታሪክ ባለሙያዎች አይክዱም የሚሉት ምሁሩ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የሀገራችን ኅልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ በመሆኑ ከልዩነቶቻችን ይልቅ ለአንድነታችን፣ ካለፈው ይልቅ ለአሁኑ፣ አጽንኦት መስጠት ይጠበቅብናል ብለው አስፍረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ኢትዮጵያውያን የተሳሰሩ፣ የተዛመዱና የተጋመዱ ናቸው፡፡ ታሪካዊ ሐቁም ይሄ ነው፡፡ ታዲያ አሁን የሰፈነው ግጭትና መገዳደል እንዴት ሊመጣ ቻለ? የሚለው ጥያቄ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያብሰለስለውና መልስ ሊያገኝለት የሚገባ ነው ብለው ጽፈዋል ኤሜሪተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ፡፡
ኢትዮጵያውያንን በታሪክ ከፍ ያደረጋቸው፣ የሚያደርጋቸውም አንድነት፣ መግባባት፣ ኅብረት እና ጽናት እንጂ ልዩነት አይደለም፡፡ ሀገር አጽንታ የኖረችውን አንድነት እንጠብቃት፡፡ ውሏንም እናጥብቃት፡፡ ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ተከብራ እንደኖረች ከእነ ክብሯ ትኖራለች፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!