የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን የደብረማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።

43

ደብረ ማርቆስ: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር ከሐምሌ/2016 ዓ.ም እስከ ጥቅምት/2017 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ከ2ሺህ 50 በላይ የሚኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በበሽታው ተጠቂ መኾናቸው ተጠቁሟል። በደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በወባ በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከባለፋት ዓመታት በተለየ ሁኔታ ከፍተኛ መኾኑን የከተማ አሥተዳደሩ ጤና መምሪያ ኀላፊ ሀብቴ ወርቁ ተናግረዋል።

ከባለፈው ተመሳሳይ ሩብ በጀት ዓመት የተመዘገበው የተጠቂዎች ቁጥር 422 የነበረ መኾኑን ያስታወሱት አቶ ሀብቴ በዘንድሮው ዓመት ግን ከ2ሺህ 50 በላይ የኾኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች በበሽታው መያዛቸውን ተናግረዋል። በሽታውን ለመከላከል በየደረጃው ከሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ጋር በመኾን ለማኅበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እየተሠራ ነውም ብለዋል።

በበሽታው የተጠቁ ሰዎች በግል እና በመንግሥት የጤና ተቋማት የሕክምና አገልግሎት እያገኙ ነው ያሉት ኀላፊው ለወባ በሽታ ሕክምና የሚውል በቂ የግብዓት አቅርቦት መኖሩንም አንስተዋል። በሽታው እየሰፋ በመኾኑ ማኅበረሰቡ ለወባ መራቢያ ምቹ የኾኑ ውኃ ያቆሩ ቦታዎችን ማፋሰስ፣ አካባቢን ማጽዳት እና አጎበርን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ከጤና ባለሙያዎች እና ከጤና ተቋማት በተጨማሪ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባ ኀላፊው አሳስበዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ከርሃብ ነጻ የኾነ ዓለም መፍጠር” በሚል መሪ መልዕክት ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
Next articleርእሰ መሥተዳድት አረጋ ከበደ በደቡብ ወሎ ዞን በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ ማሳ እየጎበኙ ነው።