
አዲስ አበባ: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ እና ጀርመን በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና በግብርና ምርቶች ላይ በጋራ ለመሥራት ሥምምነት ላይ መድረሳቸውን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) አስታውቀዋል። በጀርመን የምግብ እና እርሻ ሚኒስትር ቼም ኧዝደሚር የተመራ ልዑክ ከግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) ጋር በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና በግብርናው ዘርፍ በጋራ በሚሠሩባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ጀርመን ከ100 ዓመት በላይ ታሪካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ.ር) ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ላይ እያበረከተችው ያለው አስተዋጽኦ ለዓለም አርዓያ የሚኾን ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት የጀመረችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር አጠናክራ ትቀጥላለችም ነው ያሉት።
በግብርናው ዘርፍም ጥራት ያለው ቡናን በማምረት ኤክስፖርት እያደረገች መኾኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያ 75 በመቶ የሚኾነውን የግብርና ምርት ወደ ጀርመን እንደምትልክም ተናግረዋል። ይህም የሁለቱን ሀገራት ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎማያሲያዊ ግንኙነትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ ቡናን ወደ ጀርመን እንደምትልክ ሁሉ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ እና ምርት እና ምርታማነትን ሊያሳድጉ የሚችሉ ሜካናይዝድ የኾኑ የግብርና ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ከጀርመን መንግሥት ጋር መግባባት መደረሱንም ተናግረዋል።
የጀርመን የምግብ እና እርሻ ሚኒስትር ቼም ኧዝደሚር ዓለም በአየር ንብረት ለውጥ እየተፈተነች መኾኑን አንስተዋል። የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና ለሰው ልጅ ምቹ ዓለምን ለመፍጠር የተፈጥሮ ሃብትን መጠበቅ ብሎም መንከባከብ ይገባል ብለዋል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የሚበረታታ መኾኑን ነው የጠቆሙት።
የጀርመን መንግሥትም የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ ነው ብለዋል። ከተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራ ባሻገር በግብርናው ዘርፍም በጋራ እና በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ሥምምነት ስለመደረሱም ነው ያስገነዘቡት። በተለይም የግብርና ምርቶችን ከኢትዮጵያ ለመግዛት እና ሜካናይዝድ የኾኑ የግብርና መሳሪያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ በሚያስችሉ ጉዳዮች መግባባታቸውን ተናግረዋል።
የሁለቱ ሀገራት ሰው ሠራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎችን በጋራ ለመከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮችም እንደሚሠሩ ነው ያስረዱት። በቀጣይም የሁለቱን ሀገራት ታሪካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ዲፕሎሚያሲያዊ ግንኙነት በሚያጠናክሩ ዘርፎች በጋራ እና በትብብር እንደሚሠሩም የሁለቱ ሀገራት ሚኒስትሮች አረጋግጠዋል። ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!