
ባሕር ዳር: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በ92ኛው የኢንተርፖል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ነው። 92ኛው የኢንተርፖል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ስኮትላንድ ግላስኮው እየተካሄደ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል የተመራውና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ እና የብሔራዊ ኢንተርፖል መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ደጀኔ በቀለ ያካተተው የኢትዮጵያ ልዑክ በጠቅላላ ጉባኤው ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በጉባኤው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የድርጅቱ አባል ሀገራት የፖሊስ ኃላፊዎች፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና የተለያዩ ከፖሊስ ጋር በአጋርነት የሚሠሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እየተሳተፉ ይገኛሉ። የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታመር የድርጅቱ አባል ሀገራት ለዓለም ሰላም መስፈን በትብብር በመሥራት እያደረጉ ያሉትን ጥረት አድንቀው ሀገራቸው ለኢንተርፖል እያደረገች ያለውን ድጋፍ አጠናክራ እንምትቀጥል ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሸነር ጀነራል ኢትዮጵያ የድርጅቱን ዓመታዊ ጉባዔ እንታዘጋጅ ከኢንተርፖል ኃላፊዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ጥያቄ አቅርበዋል። የድርጅቱ ኃላፊዎችም በቀጣይ ዓመታት የሚከናወኑ የኢንተርፖል ጉባኤዎች ለአፍሪካ ወይም የድርጅቱን ጠቅላላ ጉባኤ ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ እንደሚያመቻቹ መግለጻቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
ልዑክ ቡድኑ ፖሊስ የሚገለገልባቸው ማቴሪያል እና ፖሊስ የሚጠቀምባቸውን ቴክኖሎጂ አምራች ከሆኑ እና ምርታቸውን በጉባኤው ላይ ካቀረቡ ድርጅቶች ጋር ውይይት አድርጓል። ልዑኩ በቀጣይ ቀናት ከስብሰባው ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር የሁለትዮሽ ስብሰባ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
በዓመታዊው ጠቅላላ ጉባኤ ያለፈው ዓመት የድርጅቱ ሥራ አፈጻጸም እንዲሁም በቀጣይ እቅዶች እና የተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጎ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!