
ገንዳውኃ: ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ዮሐንስ ከተማ አሥተዳደር ከሕዝቡ ጋር “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የሰላም ኮንፈረንስ ተካሂዷል። የመድረኩ ተሳታፊዎች የተገኘውን አንፃራዊ ሰላም ለማስቀጠል ሁሉም ለሰላም ሊቆም ይገባል ብለዋል።
ማንኛውም ማኅበረሰብ ታጥቀው በጫካ የወጡትን ኀይሎች በመምከር ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተሳታፊዎቹ ተናግረዋል። ሁሉም ዜጋ ሰላምን ይፈልጋል ያሉት ተሳታፊዎች ለዚህ ደግሞ ማኅበረሰቡ ሰላምን በማረጋገጥ በኩል ከመንግሥት ጎን እንደሚቆም ነው ሀሳባቸውን የሰጡት።
ልጆች እንዲማሩ፣ እናቶች በሰላም የጤና ተቋም ደርሰው እንዲወልዱ የሚያስችለውን ሰላም ለማረጋገጥ ማኅበረሰቡ ከመንግሥት ጋር በመቀናጀት ለሰላም መረጋገጥ ሊሠራ እንደሚገባም ተሳታፊዎች ጠቁመዋል። የመተማ ዮሐንስ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲቫ ሀብቴ አዲሱ ሰላምን ለማስፈን ሁሉም ማኅበረሰብ ተቀናጅቶ እንዲሠራ አሳስበዋል።
ማኅበረሰቡ የራቀውን ሰላም በማስተካከል ለልማት ዝግጁ መኾን እንዳለበትም አሳስበዋል። ልማቱም ኾነ ዕድገቱ ዕውን መኾን የሚችለው ሰላም ሲሰፍን እና ዜጎች ወደ ፈለጉት በሰላም መንቀሳቀስ ሲችሉ እንደኾነም አቶ ሀብቴ ገልጸዋል። የምዕራብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ እያሱ ይላቅ በመተሳሰብ እና በመደጋገፍ አካባቢን ብሎም ክልሉን ሰላም ማድረግ እንደሚገባ ነው ያብራሩት።
ኀላፊው ልማትን በማልማት ሀገርን ከኢኮኖሚ ውድቀት መታደግ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት። የሰሜን ምዕራብ ዕዝ የ504ኛ ኮር አስተባባሪ ብርጋዴር ጀኔራል አብደላ ሙሐመድ ማኅበረሰቡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመኾን የራቀውን ሰላም በመመለስ የሀገር ሉዓላዊነትን ማስከበር ይገባዋል ብለዋል።
በኮንፈረንሱም ጄኔራሎች፣ የአማራ ክልል የሕዝብ ቅሬታ ሰሚ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ፣ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ኀላፊ፣ የዞኑ ሰላም እና ደኅነት ምክትል ኀላፊ፣ የከተማ አሥተዳደሩ ከንቲባ፣ የሃይማኖት አባቶች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!