“ሕዝቡ መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ሊደግፍና የበኩሉን ሊወጣ ይገባል” ማማሩ አያሌው (ዶ.ር)

44

ደብረ ማርቆስ: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ)”ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሀሳብ በደጀን ከተማ ሕዝባዊ ውይይት ተካሂዷል። ከውይይቱ ተሳታፊዎች አንዷ የኾኑት ወይዘሮ ብርቱካን መንግሥቱ የደጀን ከተማ ነዋሪ ናቸው። በአነስተኛ ንግድ የቤተሰባቸውን ሕይወት ይመራሉ። ከአንድ ዓመት በፊት የተከሰተው የሰላም መደፍረስ ግን በሕይታቸው ላይ ያሳረፈው ጫና ከፍተኛ እንደኾነ ወይዘሮዋ ተናግረዋል።

ሆኖም ሰላም እንዲመጣና ያለስጋት መኖርን፣ ሠርቶ ማደርና ልጆቻቸውን ያለስጋት ማስተማር ይፈልጋሉ። ለዚህ ደግሞ የእርስ በእርስ ግጭት እና ደም መፋሰሱ በእርቅና በይቅርታ እንዲረታ እሻለሁ ብለዋል። አሚኮ ያነጋገራቸው ሌሎች የመድረኩ ተሳታፊዎችም ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የሰላም መደፍረስ ያደረሰብን ጫና ተወግዶ ሰላም እንዲመጣ የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን ብለዋል።

መንግሥት ሕግን እንዲያስከብርና በግጭት ምክንያት የተስተጓጎሉ የልማት እና የመልካም አሥተዳደር ጥያቄዎችን እንዲፈታም የውይይቱ ተሳታፊዎች ጠይቀዋል። የውይይት መድረኩን የመሩት የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ አሥተዳደሩ ከሕግ ማስከበር በተጓዳኝ በግጭት ምክንያት የተስተጓጎሉ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማነቃቃትና የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመፍታት እየሠራ ነው ብለዋል።

የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላትና ጥያቄዎቹን ለመፍታት ሰላምን ማስፈን ቀዳሚ ሥራ ነው ያሉት ዋና አሥተዳዳሪው ማኅበረሰቡ አጥፊዎችን በመገሰፅ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍንና ሰላም እንዲረጋገጥ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብለዋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጅ ቢሮ ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶ.ር) የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን የልማት ፍላጎቶች ለመመለስ በሚያደርገው ጥረት ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ እንቅፋት እንደሆነበት ተናግረዋል።

ቢሮ ኀላፊው መንግሥት ለሰላም ያለው ፅኑ አቋም ከፍተኛ ነው ብለዋል። ለዚህም ሕዝቡ መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንዲደግፍና የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል። ሕዝቡ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚሠሩ ሥራዎችን ሊደግፍ እና ፅንፈኝነትን ደግሞ ሊያወግዝ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢና የ403ኛ ኮር ዋና አዘዥ ብርጋዴል ጀኔራል አዘዘው መኮንን ሠራዊቱ የሕዝቡን ሰላም ለማረጋገጥ በትጋት እየሠራ ነው ብለዋል።

የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም ሰላማዊ አማራጭን ሊከተል እንደሚገባና ለተፈጠረው ችግር የመፍትሔ አካል በመኾን የክልሉን ሕዝብ ካገጠመው የሰላም እጦት ማላቀቅ እንደሚገባ ተመላክቷል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሕዝቡ ለሰላም ያለውን ቁርጠኛነት በተግባር አሳይቶናል” ሹመት ጥላሁን
Next articleታጥቀው በጫካ የወጡትን ኀይሎች በመምከር ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ የድርሻቸውን እንደሚወጡ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች ገለጹ።