“ሕዝቡ ለሰላም ያለውን ቁርጠኛነት በተግባር አሳይቶናል” ሹመት ጥላሁን

37

ሰቆጣ: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ወደ ነበረበት አስተማማኝ ሰላም ለመመለስ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። መላው የአማራ ክልል ሕዝብም ለክልሉ ሰላም መስፈን ያላቸውን ቁርጠኛነት በተግባር እያሳዩ ይገኛሉ።

የሰላም ኮንፈረንሱ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ባሉ ከተሞች ማለትም በሰቆጣ ከተማ፣ በጽጽቃ፣ በአምደወርቅ ከተማ እና በአስከተማ “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሣብ የሰላም መድረኮች ተካሂደዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎችም የክልሉን ሰላም ወደ አስተማማኝ ሰላም ለመመለስ መሰል መድረኮች ያላቸው ፋይዳ የጎላ መኾኑን ተናግረዋል።

የጋዝጊብላ ወረዳ ነዋሪው ቄስ ደሳለኝ ቢያድጎ የሰሜኑ ጦርነት የአካባቢውን ሃብት አውድሞ፣ የበርካታ ወጣቶችን ሕይወት ነጥቆ ሲያልፍ ተመልክተናል፤ የጦርነትን ክፋት እያወቅን ዛሬም ለዳግም እልቂት መዳረጋችን የክልሉን ጸጋ ከማውደም የዘለለ ፋይዳ የለውም ብለዋል። “እንደ ሃይማኖት አባትነቴ ስለሰላም አስተምራለሁ” ያሉት ቄስ ደሳለኝ ማኅበረሰቡም ወደ ጫካ የወጡ ልጆችን መክረው ወደ ሰላም ሊመልሷቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ መምህርት እመቤት ወርቁ “ሰላም ለሰው ልጅ ብቻ ሳይኾን ለኹሉም ፍጥረት ያስፈልጋል” ሲሉ የሰላምን አስፈላጊነት ገልጸውታል። በአካባቢያችን ያለውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል እና ከትምህርት ገበታ የራቁ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው እንዲመለሱ ሰላምን ማስፈን የውዴታ ግዴታችን አድርገን ልንተገብረው ይገባል ነው ያሉት መምህርነት እመቤት።

ወጣቶች ከስሜታዊነት ወጥተው ነገሮችን በጥሞና ማየት ይገባቸዋል ያለው ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ሻንበል ገላው ነው። እርስ በእርስ ከመገዳደል አባዜ ልንወጣ ይገባል ነው ያሉት። የጋዝጊብላ ወረዳ ዋና አሥተዳዳሪ አበባው ደሳለኝ በወረዳው አንጻራዊ ሰላም ቢኖርም በአጎራባች ወረዳዎች ሰላም ጠል የኾኑ አካላት የሚንቀሳቀሱ በመኾኑ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እንቅፋት እንደኾነ ተናግረዋል። በወረዳው ያለውን አንጻራዊ ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል ከሕዝቡ ጋር ተከታታይ የሰላም መድረኮችን እያካሄዱ እንደኾነም ጠቁመዋል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ምክትል አሥተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኀላፊ ሹመት ጥላሁን የተካሄዱ የሰላም መድረኮች በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ላለው አንጻራዊ ሰላም መስፈን ያበረከቱት አስተዋጽኦ የላቀ መኾኑን ተናግረዋል። “ሕዝቡ ለክልሉ ሰላም መስፈን ያለውን ቁርጠኛነት በተግባር አሳይቶናል” ያሉት አቶ ሹመት በቀጣይም ዘላቂ ሰላም ለማስፈን እስከ ቀበሌ ተደራሽ በመኾን የሰላም ኮንፈረንስ መድረኮች እንደሚካሄዱ ነው የተናገሩት።

የታጠቁ ኃይሎችም በሰላማዊ መንገድ ጥያቄዎቻቸውን በማቅረብ ልዩነቶችን ወደ አንድነት ለማምጣት የሰላም ጥሪውን እንዲቀበሉ አሳስበዋል። በጋዝጊብላ ወረዳ፣ ዝቋላ ወረዳ እና ድሃና ወረዳ ሲካሄዱ የነበሩ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ መድረኮች የአካባቢውን ሰላም በጋራ ለማጽናት ቃል በመገባባት በሰላም መጠናቀቃቸውን የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ አስታውቋል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ሰላም የመጀመሪያም የመጨረሻም አማራጭ እና የመፍትሔ አካል ሊሆን ይገባል” ግዛቸው ሙሉነህ
Next article“ሕዝቡ መንግሥት ሰላምን ለማረጋገጥ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ሊደግፍና የበኩሉን ሊወጣ ይገባል” ማማሩ አያሌው (ዶ.ር)