“ከገጠመን የሰላም ችግር ወጥተን ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እና በልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር ይገባል” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን

58

ደሴ: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ መልዕክት የሰላም ኮንፈረንስ በከለላ ከተማ ተካሂዷል። በኮንፈረንሱ ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በአማራ ክልል የገጠመው የሰላም እጦት ዘርፈ ብዙ ችግር አስከትሏል ብለዋል።
የሰላም ችግሩ የተከሰተው ከሰሜኑ ጦርነት ሳናገግም በመኾኑ የሕዝቡን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ማናጋቱንም አንስተዋል።

የጸጥታ ችግሩ ያስከተለው ሰብዓዊ እና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ መጠነ ሰፊ መኾኑንም አቶ አሊ ተናግረዋል። የክልሉን መንግሥታዊ መዋቅር ለማፍረስ የተደረገው ሙከራ በመከላከያ ሠራዊት እና በክልሉ የጸጥታ ኀይል መሥዋዕትነት እና ተጋድሎ ሳይሳካ መቅረቱን የገለጹት ዋና አሥተዳዳሪው ለጸጥታ ኀይሉ ድል አድራጊነት የሕዝቡ ትብብር እና ድጋፍ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው አስታውሰዋል።

የአማራ ሕዝብ ሰላም ወዳድ በመኾኑ ክልሉን ለመበታተን የተሸረበው እኩይ ሴራ ከሽፏል ያሉት አቶ አሊ ሕዝቡ ለጸጥታ ኀይሉ የሚያደርገውን ድጋፍም አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል። ክልሉን አሁን ካለበት አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ለማሸጋገር እየተሠራ መኾኑን አቶ አሊ ተናግረዋል።

መንግሥት የሚያደርገው ጥረት እንዲሳካ ሕዝቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል። የጸጥታ ችግሩን ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ በልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባም አቶ አሊ ተናግረዋል። የከለላ ከተማ ከንቲባ አስናቀው ጥላሁን የከተማ አሥተዳደሩ ሕዝብ ከወረዳው ሕዝብ ጋር በቅንጅት በመሥራት የአካባቢውን ሰላም ማስጠበቅ ችሏል ብለዋል።

የጦርነትን አውዳሚነት ከሰሜኑ ጦርነት ሕዝቡ መገንዘቡን የገለጹት ከንቲባው ክልሉ በገጠመው የጸጥታ ችግር በርካታ መሠረተ ልማቶች መውደማቸው ሕዝቡን ለከፋ ችግር እንዲጋለጥ ማድረጉን ነው የጠቆሙት። የከተማዋን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ ሕዝቡ ከጸጥታ ኀይሉ ጎን ተሰልፎ በመሥራት ለከተማዋ የልማት ሥራዎች መፋጠን የበኩሉን ሚና እንዲወጣም አሳስበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የከለላ ወረዳ እና የከለላ ከተማ አሥተዳደር ነዋሪዎች የክልሉን ሰላም መስፈን በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ውይይት መደረጉ አሁን ካሉበት የጸጥታ ችግር ለመውጣት እና የመፍትሔ አቅጣጫ ለማመላከት ያግዛል ነው ያሉት። የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደ ክልል ከጦርነት አዙሪት በመውጣት ወደ ልማት መዞር እንደሚገባም አብራርተዋል።

ሕዝቡ እስካሁን የአካባቢውን ሰላም በመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መኾኑን ያነሱት ነዋሪዎቹ በቀጣይም ከጸጥታ ኀይሉ ጎን ተሰልፎ የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመንግሥት ሠራተኞች ስለሰላም በመምከር የታቀዱ ሥራዎችን ለመፈጸም ርብርብ ማድረግ አለባቸው” አቶ ፍስሐ ደሳለኝ
Next article“ሰላም የመጀመሪያም የመጨረሻም አማራጭ እና የመፍትሔ አካል ሊሆን ይገባል” ግዛቸው ሙሉነህ