“የመንግሥት ሠራተኞች ስለሰላም በመምከር የታቀዱ ሥራዎችን ለመፈጸም ርብርብ ማድረግ አለባቸው” አቶ ፍስሐ ደሳለኝ

41

ወልድያ: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ”ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ከወልድያ ከተማ እና ከሰሜን ወሎ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች እና የቡድን የሥራ መሪዎች ጋር በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በክልሉ ያጋጠመው የጸጥታ ችግር ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን እያስከተለ መኾኑን አንስተዋል። የመንግሥት ሠራተኞች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራቸውን በአግባቡ እንዳይከውኑ ከማድረጉም ባለፈ ኅብረተሰቡ በኑሮ ውድነት እንዲሰቃይ ማድረጉን ተናግረዋል።

አሁንም የጸጥታ ችግሩ ባለባቸው አካባቢዎች በሰላም እጦት ኅብረተሰቡ እየተንገላታ በመኾኑ ከኀይል አማራጭ ይልቅ ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

በመድረኩ የተገኙት የአማራ ክልል የርእሰ መሥተዳድሩ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ ፍስሐ ደሳለኝ የመንግሥት ሠራተኞች ስለ ሰላም በመምከር በዓመቱ የታቀዱ ሥራዎችን ለመፈጸም ርብርብ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ሰላምን ለማረጋገጥ የመንግሥት ሠራተኞች ሚና ከፍተኛ በመኾኑ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማስቀጠል የሕዝባችንን የመልካም አሥተዳደር ጥያቄ ለመመለስ መሥራት ይጠይቃል ብለዋል።

እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በመለየት ኀላፊነትን በመወጣት እና ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ዘጋቢ:- ተመሥገን አሰፋ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበነፋስ መውጫ ከተማ እና ላይ ጋይንት ወረዳ አሥተዳደሮች በቅንጅት የሰላም ኮንፍረስ እየተካሄደ ነው።
Next article“ከገጠመን የሰላም ችግር ወጥተን ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ እና በልማት ሥራዎች ላይ ማተኮር ይገባል” የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን