“የአየር ንብረት ለውጥ የወቅቱ አንገብጋቢ ፈተና ነው” ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

49

አዲስ አበባ: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው የመጀመሪያ ዓለም አቀፍ ሃይድሮሜት ኮንፈረንስ ላይ ተገኝተዋል። ኮንፈረንሱ “አረንጓዴ አሻራ ለዘላቂ ቀጣናዊ የውኃ ሃብት አሥተዳደር ያለው አስፈላጊነት “በሚል መሪ መልዕክት የሚካሄድ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ የወቅቱ አንገብጋቢ ፈተና ስለመኾኑም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናግረዋል። ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ያልተጠበቁ አደጋዎች እና ንፋስ ዓለምን እየፈተናት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፍሪካ በተለይም ምሥራቅ አፍሪካ የተለየ ጫና አለበት ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ ይህንን ለመቋቋም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) አነሳሽነት ሥራዎችን እየሠራች ስለመኾኑም ነው ያስገነዘቡት።

በመድረኩ የተገኙትም በተግባር የተሠራውን ሥራ ለመግለጽ እንደኾነም አስገንዝበዋል። 40 ቢሊዮን ችግኞችን ኢትዮጵያ ስለመትከሏም አብራርተዋል። የዓለም አቀፉ የሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ፕሬዚዳንት እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የሚቲዎሮሎጂ ኀላፊ አብደላ አሕመድ (ዶ.ር) በአፍሪካ በ2023 የታየው ከባድ የአየር ንብረት ለውጥ አጅግ አስቸጋሪ ሁኔታዎች የታዩበት እንደኾነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ያሳካችውን የችግኝ ተከላ ለዚህ በመፍትሔነት የተወሰደ ትልቅ እርምጃ እንደኾነም ተናግረዋል። መንግሥታትም የውኃ ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ቅድሚያ ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ነው ያሉት። በቀጣይ የተባበሩት አረብ ኤሜሪቶች እና ሴኔጋል ለሚያስተናግዱት የተመድ የውኃ ጉባኤ ይህ ኮንፈረንስ እንደግብዓት ኾኖ ያገለግላል ብለዋል።

በኮንፈረንሱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኀላፊዎች አምባሳደሮች እና የዘርፉ ምሁራን ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፦ አንዱዓለም መናን

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየደምበጫ ዙሪያ ወረዳን ሰላም ለማረጋገጥ የነዋሪዎች ሚና ትልቅ መኾኑ ተገለጸ፡፡
Next articleየሉማሜና አካባቢው ነዋሪዎች በወቅታዊ የሰላም ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያካሄዱ ነው።