በፀጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጡ የልማት ሥራዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ወጣቱ ለሰላም እንዲሠራ የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር አሳሰበ፡፡

39

ደብረ ማርቆስ: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በደብረማርቆስ ከተማ አሥተዳደር በወቅታዊ ሰላም እና ደኅንነት ዙሪያ በከተማዋ ከሚገኙ ወጣቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል። በውይይት መድረኩም ሰላም፣ የኑሮ ውድነት እና ልማት ትኩረት የተሰጠባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎችም ሰላም እንዲሰፍን መንግሥት በትኩረት ሊሠራ ይገባል ነው ያሉት።

በከተማዋ የሚስተዋለው የሰላም መደፍረስ በሥራ ዕድል ተጠቃሚነታቸው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩንም አንስተዋል። በከተማዋ ከሚደረጉ ተደጋጋሚ ውይይቶች ባለፈ መሬት ላይ የሚወርድ ተጨባጭ ሥራ ያስፈልጋልም ብለዋል።

የወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማስፋት በፀጥታ ችግር ምክንያት የተቋረጡ የልማት ሥራዎችን ወደ ሥራ እንዲገቡ ወጣቱ ለሰላም መስፈን ትልቅ ሚና ሊወጣ እንደሚገባም ነው የደብረ ማርቆስ ከተማ ምክትል ከንቲባ ስለሺ ተመሥገን የተናገሩት።

በመድረኩ የተገኙት የደብረ ማርቆስ ከተማ አሥተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መልካሙ ሽባባው የከተማዋን ሰላም ለማረጋገጥ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን መለየት እና ከፀጥታ አካሉ ጋር በጋራ መሥራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

ወጣቱ ምክንያታዊ በመኾን የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ማቅረብ እንዳለበትም አንስተዋል።

በውይይት መድረኩ በከተማዋ ከሚገኙ አራቱም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሰላም ሚኒስቴር እና የመሀመድ ቢን ዛይድ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት አደረጉ።
Next articleየምድረ ገነት ከተማ ነዋሪዎች ሰላምን ሊያረጋግጡ ይችላሉ ባሏቸው ጉዳዮች ላይ መከሩ፡፡