
ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ ያዘጋጀችውን ዓለም አቀፍ የሃይማኖት ተቋማት ኮንፍረንስ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ፣ የሰላም ሚኒስትሩ ብናልፍ አንዱዓለም እና የመሐመድ ቢን ዛይድ ዩኒቨርሲቲ ቻንስለር ከሊፋ ሙባረክ (ዶ.ር) ከፍተውታል።
ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በመድረኩ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር “ኢትዮጵያ ለዘመናት በሃይማኖቶች መካከል መቻቻልን እና አብሮ መኖርን ያሳየች ሀገር ናት” ብለዋል።
ኢትዮጵያ ክርስትናን እና እስልምናን ቀድማ የተቀበለች ሀገር መኾኗን በመጥቀስ በሀገሪቱ ያለውን የሃይማኖቶች መቻቻል አንስተዋል።
ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ብዝኅነት የተቀበለች ሀገር ናት ያሉት ፕሬዚደንቱ ሃይማኖት ተቋማቱ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሚናቸው የላቀ መኾኑንም አንስተዋል።
የሃይማኖቶች መቻቻል እና በጋራ መኖር የምንናፍቃትን ዓለም እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ በዓለም ጽንፈኝነት ዙሪያ በሃይማኖት ተቋማት በኩል መፍትሄ ሊፈለግለት ይገባል ብለዋል።
ሃይማኖት በዜጎች መካከል መከፋፈልን ለማስወገድ ድልድይ ኾኖ እንደሚያገለግል ጠቅሰው ጠንካራ የኾነ አንድነትን ለማምጣት ከሃይማኖት ተቋማት ትልቅ ሚና እንደሚጠበቅም መግለጻቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!