
እንጅባራ: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በቻግኒ ከተማ “ሰላም ለሁሉም፣ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ በወቅታዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የሚመክር ሕዝባዊ የውይይት እየተካሄደ ነው፡፡ በውይይቱ ከከተማ አሥተዳደሩ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ተሳትፈዋል፡፡
የአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ቴዎድሮስ እንዳለው በክልሉ ብሎም በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀው የፀጥታ ችግር ዜጎች ለዘመናት የገነቧቸው የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴቶች እንዲሸረሸሩ አድርጓል ብለዋል። ኅብረተሰቡ አንድነት እና ወንድማማችነትን የሚፈታተኑ ከፋፋይ ድርጊቶችን አምርሮ በመታገል የቀደመ አብሮነቱን አጠናክሮ ማስቀጠል እንዳለበትም ዋና አስተዳዳሪው አሳስበዋል።
የቻግኒ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ እና የከተማና መሰረተ ልማት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገበየሁ አልማው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በርካታ ውስብስብ ችግሮች አጋጥመዋል ብለዋል። ነገር ግን በመሪው፣ በፀጥታ አካሉ ቁርጠኝነት እና በኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ ማኀበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ሳይስተጓጎሉ ማስቀጠል መቻሉን ገልጸዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ አሁንም አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የሰዎች እገታ፣ ዝርፊያ እና ሕገ ወጥ የተኩስ ወንጀሎች እየተፈፀሙ መኾኑንም ጠቁመዋል። በድርጊቱ እጃቸው ያለበት አካላትን በመለየት የሕግ ተጠያቂነትን ለማስፈን እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል። በመሪዎች፣ በፀጥታ መዋቅሩ እና በኅብረተሰቡ እልህ አስጨራሽ ትግል የተገኘው የሰላም ተስፋ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሕዝቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የሰላም ዘብ ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችም ደስታና ሀዘንን ተጋርተው ዘመናትን ያሳለፉባት የብሔር ብሔረሰቦች መዲና ቻግኒ ሰላሟ እንዲታወክ አንፈቅድም ነው ያሉት። ከአንድ አመት በላይ የዘለቀው የፀጥታ ችግር የዜጎችን ነፃ እንቅስቃሴ ከመገደብ፣ በዘመናት ድካም ያፈሩት ሃብት እንዲወድም፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉ ከማድረግ ውጭ የፈየደው ነገር አለመኖሩን ያነሱት ተሳታፊዎቹ የችግሮች ሁሉ መፍቻ ሰላማዊ ውይይት መኾን እንዳለበት ገልጸዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!