የተገኘውን ሰላም በዘላቂነት ለማስቀጠል በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልግ የጋዝጊብላ ወረዳ አሥተዳዳሪ ተናገሩ።

13

ሰቆጣ: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ወደነበረበት ለመመለስ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። ሕዝቡም ለሰላም ያለውን ቁርጠኛነት እየገለጸ ይገኛል። ዛሬም በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጋዝጊብላ ወረዳ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ እየተካሄደ ነው።

በጋዝጊብላ ወረዳ አስከተማ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ መድረክ የከፈቱት የወረዳው ዋና አሥተዳዳሪ አበባው ደሳለኝ ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የእርስ በእርስ ጦርነት ካደረሰብን ኪሳራ ሳናገግም ዳግም እርስ በእርስ መፋጀት ትርፉ ውድመት መኾኑን መገንዘብ ይገባናል ብለዋል።

“በአካባቢያችን የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች ከእኛው የወጡ ናቸው” ብለዋል አሥተዳዳሪው። ልጆቻችንን በመምከር ወደ ሰላም እንዲመጡ ልናደርጋቸው ይገባል ሲሉም አሳስበዋል። በመዳፋችን ውስጥ ያለውን ሰላም ከመዳፋችን እንዳይወጣ መጠበቅ ከሁላችን የሚጠበቅ ተግባር ነው በማለት ማኅበረሰቡ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጥ አሳስበዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ምክትል አሥተዳዳሪና የኢንቨስትመንት መምሪያ ኃላፊ ሹመት ጥላሁን፣ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ዳግም ባይነሳኝ እና የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ሃምሳ አለቃ አዘዘው አዳነ ውይይቱን እየመሩ ነው።

በውይይቱም የጋዝጊብላ ወረዳ መሪዎች፣ የአስከተማ ከተማ ነዋሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች እና ታዋቂ ሰዎች ተሳታፊ ናቸው። በሕዝባዊ ውይይቱም የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ የሚያስችል የጋራ መግባባት ላይ ይደረሳል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ:- ደጀን ታምሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበመስኖ ልማት ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት አቅዶ እየሠራ መኾኑን የምሥራቅ ጎጃም ዞን አስታወቀ።
Next article“መንግሥት በወሰደው የሰላም ቁርጠኝነት እና በሕዝቡ ትብብር የተገኘውን ሰላም ዘላቂነት ለማረጋገጥ የሁላችንም ኀላፊነት ሊኾን ይገባል” ማማሩ አያሌው (ደ.ር)