
ደሴ: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ)
በደቡብ ወሎ ዞን ሃርቡ ከተማ ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከተውጣጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ጋር የሰላም ውይይት እየተካሄደ ነው።
በውይይት መድረኩ ከከተማዋ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች እንዲኹም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።
በመድረኩ መጀመሪያ ላይ መልእክት ያስተላለፉት በብልፅግና ፓርቲ የሃርቡ ከተማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጀማል ኑሩ “በፀጥታ ችግር ብንፈተንም ከሕዝባችን ጋር በጋራ በመሥራት የከተማችንን ሰላም ማስጠበቅ ችለናል” ብለዋል። የተገኘውን ሰላም ለማፅናት አሁንም ብዙ ሥራዎች ይጠብቁናል ሲሉ ገልጸዋል።
የክልሉ ሕዝብ ማኅበራዊ እረፍት አጥቶ ለከፍተኛ እንግልት ተዳርጎ መቆየቱን የገለጹት ኀላፊው ሀገር እና ሕዝብ የማውደም አጥፊ ተግባሮችን በመታገል ይገባል ብለዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኀላፊው መሐመድ አሊ የሰላም ባለቤት የሆነው ሕዝብ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር ሰላምን ለመጨረሻ ጊዜ ለማፅናት ሊሠራ ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።
እንደ ክልል የፀጥታ ችግር ከገጠመን ጊዜ ጀምሮ በዞኑ ሰላምን ለማፅናት ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መከናወናቸውን በማስታወስ አሁንም በችግሩ ምንጭ ላይ በግልፅ መግባባት ላይ በመድረስ ሰላማችንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማፅናት ይገባል ነው ያሉት::
በውይይቱ መድረኩ በተለይ ሰላምን በማፅናት በኩል በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሩያ በግልፅ ከመወያየት ባለፈ መፍትሄም በማስቀመጥ እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።
ዘጋቢ:- ደምስ አረጋ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!