
ባሕር ዳር: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል በዚህ ዓመት ከ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በዘር በመሸፈን 169 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማምረት ሢሠራ መቆየቱን በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ኀላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) ገልጸዋል።
የሰብሉ ቁመና ጥሩ ደረጃ ላይ መኾኑን እና የታቀደውን ለማሳካት እንደሚያስችል የቁም ሰብል ግምገማው ያሳያል ብለዋል። ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጨመረ በመምጣቱ የምርት ብክነት እንዳይከሰት እና ምርት እንዳይበላሽ መላው የክልሉ አርሶ አደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎች እና መሪዎች እጅ እና ጓንት ኾነው የሰብል ሥብሠባ ሥራውን እንዲያከናውኑም አሳስበዋል።
ቀድመው የደረሱ በተለይ እንደ ማሾ፣ ሰሊጥ፣ ጤፍ፣ ስንዴ፣ እና ገብስ የመሳሰሉ ሰብልን ያልታጨዱትን በማጨድ እና የታጨደው ደግሞ ተወቅቶ በፍጥነት ወደጎተራ እንዲገባ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። በዚህ ወቅት የሚጥለው ዝናብ የቀጣይ የመስኖ ሥራዎችን ለማከናወን እና ቀድመው ያልደረሱ ሰብሎች የውኃ እጥረት እንዳይገጥማቸው የሚያግዝ ቢኾንም በአብዛኛው ግን ጉዳቱ ያመዘነ እንደኾነ ነው ያብራሩት።
በመኾኑም የደረሰ ሰብልን ቀድሞ መሠብሠብ፣ የተሠበሠበን ሰብል ደግሞ መሬት ላይ ከማስጣት ይልቅ ከመሬት ከፍ አድርጎ መከመር እና የውቂያ ሥርዓቱም የምርት ብክነት በማያመጣ መንገድ መኾን አለበት ነው ያሉት። ዶክተር ድረስ የድኅረ ምርት ብክነት እንዳይከሰት በኩታ ገጠም የተዘሩ ሰብሎችን በኮምባይነር መሠብሠብ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ሰሞኑን በምሥራቅ አማራ ደቡብ ወሎ፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አሥተዳደር እና በሰሜን ሸዋ ዞን የተወሰኑ ወረዳዎች ላይ የግሪሳ ወፍ መከሰቱን ያነሱት ዶክተር ድረስ በአውሮፕላን ርጭት መቆጣጠር መቻሉን አንስተዋል። ቢጫ ዋግ እና ተባይ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የክትትል እና ቁጥጥር ሥራ መሠራት እንዳለበትም አሳስበዋል።
ወቅቱ የግብርና ሥራ ትልቅ መታጠፊያ በመኾኑ በክልሉ የገጠመውን የሰላም ችግር በመቅረፍ መላ ሕዝቡ ፊቱን ወደልማት እንዲያዞር ማድረግ አለብን ሲሉም አሳስበዋል። ዋናው ጠላት ድህነት መኾኑን በመገንዘብ ድህነትን ለመፋለም መላው ሕዝብ እጅ ለእጅ ተያይዞ መሥራት አለበትም ብለዋል።
በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችም ተከታታይ ድጋፍ እና ክትትል ለማድረግ ዝግጁ መኾናቸውን የግብርና ቢሮ ኀላፊው ዶክተር ድረስ አረጋግጠዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!