
ጎንደር: ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ ክልል ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከሐምሌ/2016 ዓ.ም እስከ ጥቅምት/2017 ዓ.ም ባሉት ወራት ውስጥ ከ43 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል።
መምሪያው ከሐምሌ/2016 ዓ.ም ጀምሮ ከ102 ሺህ በላይ ለሚኾኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምርመራ በማድረግ ከ43 ሺህ በላይ በወባ የተጠቁ ግለሰቦችን ማግኘቱ እና የሕክምና ክትትል ማድረጋቸውን የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኀላፊ ስማቸው ግደይ ገልጸዋል።
ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ25 በመቶ ጭማሬ ማሳየቱን የገለጹት አቶ ስማቸው ባለፈው ሳምንት ብቻ ከ4 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ገልጸዋል።
ከ2 ሺህ በላይ አጎበርን ለኅብረተሰቡ ማሰራጨት ተችሎ እንደነበር አንስተዋል። ምክትል ኀላፊው አካባቢው በየዓመቱ ከ500 ሺህ በላይ የቀን ሠራተኞች ለምርት ሥብሠባ ስለሚመጡ የወባ ስርጭት መጠኑ መስፋቱን አንስተዋል።
የወባ መድኃኒት አቅርቦት እጥረት እንዳለ የተናገሩት አቶ ስማቸው ችግሩን ለመቅረፍ ከጤና ቢሮ ጋር በቅርበት እየተሠራ ነው ብለዋል።
የወባ ስርጭት ሂደቱን ለመቆጣጠር ከማኅበረሰቡ ጋር በመተባበር ውኃ የሚያቁሩ ቦታዎችን የማጽዳት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን ተናግረዋል። ችግሩን ለመቅረፍ ማኅበረሰቡ የራሱን ጥንቃቄ እንዲያደርግም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!